አሜሪካ፡ ሜላኒያ ትራምፕ በትውልድ አገሯ ሐውልት ቆመላት

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ትውልድ አገሯ አሜሪካ ሳይሆን ስሎቬኒያ ነው።
ተወልዳ ባደገችበት ሰፈር አቅራቢያ ከነሐስ የተቀረጸ መጠነኛ ሐውልት ቆሞላታል።
ከዚህ በፊት በእንጨት የተሠራ በተወሰነ ደረጃ የቧልት የሚመስል ሐውልት ቆሞላት ነበር።
አንድ ሰው በሐውልቱ ጥራት ተበሳጭቶ ይሆን ወይም በሌላ ብቻ እሳት ለኮሰበትና ወደመ።
ይህ የሆነው ባለፈው ዓመት ነበር።
አንዳንዶች ያንን የእንጨት ሐውልት ‹‹ክብረነክ›› ብለው ነበር የሚጠሩት።
ሐውልቱ ከኪነ ሐውልት አንጻር ቀሽም መሆኑ ብቻ ሳይሆን ቀዳማዊት እመቤቷን የሚመስል አንዳችም ነገር አልነበረውም ተብሏል።
የአሁኑ ከዚያ የተሻለ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለቤት ሜላኒያ ትራምፕ የተወለደቸው በ1970 በስሎቬኒያ ኖቮ ሜስቶ በምትባል አካባቢ ነው፡፡ የከተማዋ ስም ሰቭኒካ ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡
ያን ጊዜ ስሎቬኒያ የኮሚኒስት ዩጎዝላቪያ አካል ነበረች።
ትናንት ማክሰኞ ከነሐስ የተሠራው አዲሱ ሐውልቷ የተመረቀው በትውልድ ሰፈሯ ሲሆን የድሮውን የተቃጠለ ሐውልት የሚተካ ይሆናል ተብሏል፡፡
"ዛሬ እዚህ የተገኘነው የሜላኒያን የተቃጠለ ሐውልት መልሰን በማቆማችን ነው" ብሏል የስሎቬኒያ ቀራጺ ቪቮዳ ለአሶሲየትድ ፕሬስ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑ ወዲህ ቱሪስቶች የቀዳማዊት እመቤቷን ትውልድ ከተማ ለማየት ሲሉ ወደ ሰቭኒካ መምጣት ጀምረዋል፡፡
በምረቃው ላይ ነዋሪዎች ዶናልድ ትራምፕ የሚወዱትን በርገር፣ እንዲሁም የሷ ምሥል ያለበትን ኬክና ቲሸርቶች ይዘው ተገኝተዋል፡፡
የሜላኒያ ወደ አሜሪካ ያቀናችው በፋሽን ሞዴልነት በ1996 ሲሆን ከ2 ዓመት በኋላ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በአንድ ፓርቲ ተገናኝተው ተዋወቁ፡፡
እንደ አውሮጳዊያኑ በ2005 ተጋቡ፡፡ በዓመቱ ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሙንም ባሮን አሉት፡፡ ሚሊያና ለትራምፕ 3ኛ ሚስታቸው ናት፡፡
የእርሷ ዕድሜ አሁን 50 ሲሆን እሳቸው 74 እያለፉ ነው፡፡
ሜላኒያ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ውጭ አገር ተወልዳ ቀዳማዊት እመቤት ለመሆን 2ኛዋ ሴት ናት፡፡
































