በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ነው

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመጋቢት ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛ ጭማሬ ያሳየው በባለፉት ሁለት ሳምንታት ሲሆን፤ በሃገሪቱም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2ሺህ 156 ደርሷል። ከነዚህም መካከል 361 ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 27 መድረሱን የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ በቫይረሱ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭዎች ቁጥርም ማሻቀቡ የተገለፁ ሲሆን ከሰሞኑም 97 የጤና ተቋም ሰራተኞች በቫይረሱ ተይዘዋል።ከህሙማን ጋር ንክኪ ነበራቸው የተባሉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር 2340 ደርሷል። ኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሌም ቢሆን ከንክኪ በኋላ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የእርስዎንም የሌሎችን ጤና ይጠብቃል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን እየመዘገቡ

    Route 66

    በአሜሪካ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ፍጥነት መጠን እየቀነሰ ነው ቢባልም በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ግን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች አማካይ ቁጥር እየጨመረ ነው።

    እንደ ዋሽንግተን ፖስተ ሪፖርት ከሆነ 14 የአሜሪካ ግዛቶች ከፍተኛ የሆነው የሰባት ቀናት አማካይ ቁጥር መዝገበዋል።

    ከፍተኛ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ላይ ጭማሪ ከመዘገቡ ግዛቶች መካከል፤ አላስካ፣ አሪዞና፣ አርካንሳስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ፍሎሪዳ፣ ኬንታኪ፣ ኒው ሜክሲኮ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ሚሲሲፒ፣ ኦሬገን፣ ሳውዝ ካሮላይና፣ ቴኔሲ፣ ቴክሳስ እና ዩታህ ተጠቃሽ ናቸው።

    የተጠቀሱት ግዛቶች ጥብቅ የሆነ ማኅበራዊ ርቀትን ማስጠበቅ ያልቻሉ ግዛቶች ናቸው ተብለዋል።

    የቫይረሱ ስርጭት በአሜሪካ መስፋፋት ከጀመረ ወዲህ ትናንት በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ያገኘችው ሳውዝ ካሮላይና ግዛት፤ ስፖርት ቤቶችን፣ ምግብ ቤቶች እና የውበት መጠበቂያ ሳሎኖችን ክፍት አድርጋለች።

    በአሜሪካ አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው።

  2. የብራዚል ፍርድ ቤት በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ይፋ እንዲሆን ወሰነ

    ብራዚል

    የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአገሪቱ ጤና ሚንሰቴር በኮረናቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን እንደገና እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጠ።

    የብራዚል ጤና ሚንስቴር በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎችን አሃዝ የሚያሳይ ገጽን በሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ካነሳ በኋላ በቫይረሱ የሚሞቱ እና የሚያዙ ሰዎች አጠቃላይ አሃዝ ከአሁን በኋላ ይፋ አላደርግም ብሎ ነበር።

    የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አሌክሳንደር ዲ ሞራኤስ የመንግሥት ውሳኔ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ አድርጎታል፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠርም በቂ እርምጃ እየወሰደ አይደለም ብለዋል።

    የጤና ሚንስቴር አጠቃላይ አሃዞችን ይፋ አላደርግም የሚለው ውሳኔ በፕሬዝደንት ጄይረ ቦልሶናሮ ላይ ከፍተኛ ትችትን አስነስቷል። ፕሬዝደንቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በቂ እርምጃ እየወሰዱ አይደለም እየተባሉ በተደጋጋሚ ይተቻሉ።

    በቅርቡም ከቦልሶናሮ ጋር መስማማት ያልቻሉ የጤና ሚንስትሮች ስልጣናቸው ሲለቁ ነበር።

    ቦልሶናሮ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉ የብራዚል ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋር በተደጋጋሚ ሲጋጩ ነበር። ቦልሶናሮ "የእንቅስቃሴ ገደብ ምጣኔ ሃብታችንን ይጎዳል" በማለት የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲኖር አይሹም።

    ብራዚል እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን ከ37 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

  3. በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 200 ሺህ እየተጠጋ ነው

    ጥሪ

    በአፍሪካ ውስጥ ኮሮናቫይረስ ከሌላው ዓለም ዘግይቶ ቢከሰትም አሁን ግን በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በፍጥነት እየጨመረ ነው።

    በእያንዳንዱ የአፍረካ አገር ውስጥ በየደቂቃው በኮቪድ-19 የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎችን አሃዝ እዚህ ይመልከቱ፡በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ክስተት መከታተያ ካርታ

  4. የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አጋጥሞት የማያውቀው ኪሳራ ደርሶበታል ተባለ

    Cathay Plane

    የዓለም አቀፉ አየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) የዚህ ዓመት አጠቃላይ የአየር መንገዶች ገቢ እአአ 2019 ላይ ከተመዘገበው በ419 ቢሊየን ዶላር ይቀንሳል ብሏል።

    ይህ አሃዝ ማህበሩ ከዚህ ቀደም ካስቀመጠው ቅድመ ግምት በ100 ቢሊየን ዶላር ጨምሯል።

    የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር እንደሚለው ከሆነ አየር መንገዶች 84 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ያጋጥማቸዋል።

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በማለትም መንግሥታት ደንበሮቻቸውን ዝግ ማድረጋቸውን ተከትሎ የበረራ ኢንደስትሪው አይቶት የማያውቀው ኪሳራ አጋጥሞታል ይላል።

    በሚያዚያ ወር የበረራ መጠን በ95 በመቶ መቀነሱ ተጠቁሟል። ይህም በኢንደስትሪው ታይቶ የማይታወቅ ዝቅተኛ መጠን ነው ብሏል ማህበሩ።

  5. በስፔን በሽታው እስኪጠፋ ድረስ ጭምብል ግዴታ ሆኖ ይቆያል

    የሙቀት ልኬት

    የስፔን ጤና ሚኒስትር ሳልቫዶር ኢላ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አስኪጠፋ ድረስ በአገሪቱ የተጣለው ጭምብል የማድረግ ግዴታ ጸንቶ እንደሚቆይ አስታወቁ።

    የአፍና የአፍናጫ መሸፈኛ ጭንብል የማድረግ ውሳኔው “ለወረርሽኙ መከላከያ ክትባት ወይም ፈዋሽ መድኃኒት ተገኝቶ በሽታውን በአስተማማኝ ሁኔታ ማሸነፍ አስኪቻል ድረስ ይቀጥላል” ብለዋል።

    ከግንቦት መጨረሻ ጀምሮ ስፔን ውስጥ ከስድስት ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ ሰዎች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸውና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይቻልባቸው ቦታዎች ላይ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ሆኗል።

    ከሁለት ሳምንት በኋላ በስፔን የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በይፋ የሚያበቃ ሲሆን ግዴታዎች ግን ባሉበት የሚቆዩ ሲሆን ተግባራዊ የማያደርጉ ሰዎች 100 ዩሮ ይቀጣሉ።

    ኮሮናቫይረስ ስፔን ውስጥ ከ27 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን አሁን ግን በቁጥጥር ስር ስላዋለች፤ ጥላቸው የነበሩ ገደቦችን የማላላት እርምጃ እየወሰደች ነው።

  6. ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም ከኮሮናቫይረስ ይጠብቀናል?

  7. ምልክት የማያሳዩ ቫይረሱን የማስተላለፍ እድላቸው 'በጣም ጠባብ ነው ተባለ

    WHO Technical Lead Maria Van Kerkhove

    ኮሮናቫይረስ ኖሮባቸው የበሽታውን ምልክት ግን የማያሳዩ ሰዎች ቫይረሱን ወደሌሎች የማስተላለፋቸው አጋጣሚ "በጣም አነስተኛ ነው" ተባለ።

    የዓለም ጤና ድርጅት የቴክኒክ መሪ የሆኑት ዶ/ር ማሪያ ቫን ኬርክሆቭ እንዳሉት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ንክኪ ለማጣራት በተደረገው ጥረት፤ ቫይረሱ እያለባቸው ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ቫይረሱን የማስተላለፋቸው እድል ዝቅተኛ መሆኑን ተረድተናል ብለዋል።

    ቫይረሱ እያለባቸው ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ማለት፤ ኮሮናቫይረስ እያለባቸው የበሽታው ምልክት የሆኑት እንደ ደረቅ ሳል፣ ትኩሳት፣ የምግብ እና መጠጥ ጣዕም ማጣት የመሳሰሉት ምልክቶች የማያሳዩ ማለት ነው።

    ቴክኒካል ዳይሬክተሯ እንዳሉት ከዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መልክት ማሳየት ሊጀምሩ ሲሉ ግን ቫይረሱን ወደሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

  8. ኮሮናቫይረስ በቻይና ከተባለው ጊዜ ቀድሞ መከሰቱን የሳተላይት ምስሎች ጠቆሙ

  9. ቻይና ወደ አውስትራሊያ የሚሄዱ ዜጎቿን አስጠነቀቀች

    2019 ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ተማሪዎች በአውስትራሊያ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነበር።
    የምስሉ መግለጫ, 2019 ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ተማሪዎች በአውስትራሊያ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነበር።

    ቻይና ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ከግምት በማስገባት ዜጎቿ ለትምህርት ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ ከመወሰናቸው በፊት ውሳኔያቸውን ዳግም እንዲያጤኑት አሳሰበች።

    ከቻይና የትምህርት ሚንስቴር የተሰጠው መግለጫ፡ "በወረርሽኙ ወቅት በአውስትራሊያ የእስያ ዝርያ ያላቸው ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ በርካታ የዘር ጥቃቶች ተፈጽመዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር ስላልዋለ በጉዞ ወቅት እና በትምህርት ቤቶች ቅጥር ጊቢ ውስጥ ለበሽታው የመጋለጥ እድል ይኖራል" ይላል።

    ከወራት በፊት አውስትራሊያ የቫይሱ ትክክለኛ መነሻ ምንጭ ምን እንደሆነ በገለልተኛ አካል ይጣራ ስትል መጠየቋ ይታወሳል።

    የአውስትራሊያው የትምህርት ሚንስትር ዳን ቴሃን በበኩላቸው፤ የቻይና አቻቸው አውስትራሊያን በማስመልከት የሰጠው መግለጫ ስህተት ነው ብለዋል።

    ሚንስትሩ አውስትራሊያ ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች ተመራጭ መዳረሻ ነች ያሉ ሲሆን፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ ስኬታማ ስለሆንን፣ የተለያየ ባህል ያላቸው ተማሪዎች ስለሚገኙ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟላ ትምህርት ስለምንሰጥ ነው ብለዋል።

    ሚንስትሩ ጨምረውም "በዓለም ላይ ከሚገኙ የተማሪዎች ደህንነትን ከሚያረጋግጡ አገራት መካከል ተጠቃሽ ነን" ብለዋል።

    እአአ 2019 ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ተማሪዎች በአውስትራሊያ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነበር።

  10. "ቤት የመቀመጥ ግዳጅ ባይሆን በአውሮፓ 3 ሚሊዮን ሰዎች ይሞቱ ነበር" ጥናት

  11. ደቡብ አፍሪካ ለኩባ ዶክተሮች 14 ሚሊዮን ዶላር ልትከፍል ነው

    የኩባ ጤና ባለሙያዎች ደቡብ አፍሪካ ሲደርሱ
    የምስሉ መግለጫ, የኩባ ጤና ባለሙያዎች ደቡብ አፍሪካ ሲደርሱ

    ደቡብ አፍሪካ ለ187 የኩባ ዶክተሮች 14 ሚሊዮን ዶላር ልትከፍል መሆኑ ተነገረ።

    የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር ዝዌሊ ማክሂዜ እንዳሉት አገሪቱ በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎቿን እንዲያክሙ ላስመጣቻቸው የኩባ ዶክተሮች 14 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይኖርባታል ብለዋል።

    የጤና ሚኒስትሩ እንዳሉት 187 የጤና ባለሙያዎች እስከ 2021 (እአአ) በደቡብ አፍሪካ ይቆያሉ።

    የጤና ሚንስትሩ እንደሚሉት ከሆነ፤ በተለያየ የጤና ዘረፍ የሰለጠኑት የሐኪሞች ቡድን አባላት ወደ ደቡብ አፍሪካ ማስመጣት ያስፈለገው፤ አገሪቱ በዘረፉ ያስፈልጓት የነበሩ ባለሙያዎች በበቂ ቁጥር ስላልነበራት ነው ብለዋል።

    የጤና ባሉያዎቹ ከኩባ ተጉዘው ደቡብ አፍሪካ እንዲመጡ መደረጋቸው በርካቶችን ያስደሰተ አልነበረም። በሥራ ፍለጋ ብዙ እየደከሙ ለሚገኙ የደቡብ አፍሪካ ሥራ ፈላጊ የጤና ባለሙያዎች ቅድሚያ መሰጠት ነበረበት የሚሉት በርካቶች ናቸው።

  12. 'ተርማል ካሜራ' ኮሮናቫይረስ ያለበትን ሰው የመለየት አቅም አላቸው?

    thermal cameras

    የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ተጥለው የነበሩ ገደቦች እየተነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ በርካቶች 'ተርማል ካሜራዎችን' (የሰውነት ሙቀት መለኪያዎችን) በመጠቀም ሰዎች ሕዝብ ወደሚበዛበት ቦታ ከመቀላቀላቸው በፊት የሰውነት ሙቀት ሲለኩ ይስተዋላል።

    የኢንፍራሬድ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙት 'ተርማል ካሜራዎች' አብዛኛውን ጊዜ ከግንባራችን ላይ ሙቀትን በመለካት የሰውነት ሙቀት ግምት ይሰጣሉ።

    ከዚህ ቀደም መሰል የኢንፍራሬድ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ቁሶች የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተዳፍኖ የሚገኘን እሳት ለይቶ ለማግኘት እንዲሁም ፖሊሶች ከዓይን እይታ ውጪ ተደብቆ የሚገኘን ሰው ለይቶ ለማግኘት ይጠቀሙበት የነበረ ቁስ እንጂ እንደ የህክምና ቁስ አገልግሎት ላይ ውሎ አያውቅም።

    በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴሪክ ሂል እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ኢንፍራሬድ ካሜራዎች የህክምና ቁስ አይደሉም፤ የሚሰጡት የሰውነት ሙቀት መጠንም ግምታዊ እንጂ እንደ ቴርሞሜትር ለትክክለኛው አሃዝ የቀረበ አይደለም ይላሉ።

  13. ሰበር, በኢትዮጵያ ተጨማሪ 190 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ

    bb

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 190 ሲሆን ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው። ይህም ኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 2336 ከፍ አድርጎታል።

    የጤና ጥበቃ እና የማህብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ለ4599 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል።

    ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋጋጡት መካከል 153 የሚሆኑት የተገኙት ከአዲስ አበባ ከተማ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል።

    ከዚሀ በተጨማሪ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ምክንያት የ5 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ወደ 32 ከፍ አድርጎታል።

  14. ማልታ ለዜጎቿ ምግብ እና መጠጥ መግዣ የሚሆን 100 ዩሮ ልታድል ነው

    Malta

    የማልታ መንግሥት ከ16 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎቹ በሙሉ 100 ዩሮ የሚያወጡ ምግብ እና መጠጥ መግዣ ኩፖን ሊያድል መሆኑ ተሰምቷል።

    ዜጎች ባለ 20 ዩሮ ዋጋ ያላቸውን አምስት ኩፖኖች መጠቀም የሚችሉት በምግብ ቤቶች እና በመጠጥ ቤቶች ውስጥ ብቻ ነው ተብሏል።

    መንግሥት ይህ ለማድረግ የወሰነው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ተገድቦ የነበረውን እንቅስቃሴ በማላላት ዜጎች ወደ ቀደመ ኑሯቸው በፍጥነት እንዲመለሱ ለማበረታታት ነው ተብሏል።

    በሰሜናዊ አፍሪካ እና ጣሊያን መካከል የምትገኘው አውሮፓዊቷ አገር ማልታ፤ አንድ አራተኛ የሚሆነው አጠቃላይ ገቢዋን የምታገኘው ከቱሪዝም ዘረፍ ነው።

    ከመስከረም ወር በኋላ ደግሞ በቱሪዝም ዘረፍ ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች ለእያንዳንዳቸው የ800 ዩሮ ድጎማ ይደረጋል ተብሏል።

    • የጆሃንስበርግ ከንቲባ ራሳቸውን አገለሉ

      ከንቲባ ጂኦፍሬይ ማኩሁቦ
      የምስሉ መግለጫ, ከንቲባው ከዚህ ቀደም ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ ሆነዋል

      የደቡብ አፍሪካዋ ንግድ ማዕከል ጆሃንስበርግ ከተማ ከንቲባ አንድ የመሥሪያ ቤታቸው ሰራተኛ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ራሳቸውን አገለሉ፡፡

      ከከንቲባው ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ ከንቲባ ጂኦፍሬይ ማኩሁቦ፤ የምርመራ ውጤታቸው እስከሚታወቅ ድረስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ እንደሚገኙ አትቷል፡፡

      ከዚህ በፊትም ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን መግለጫው አስታውሷል፡፡

      አሁን አዲስ የጽ/ቤቱ ሰራተኛ በቫይረሱ መያዙን ተከትሎ ሁሉም ሰራተኞች ምርመራ አድርገዋል፡፡

      "ከንቲባው ራሳቸውን አግልለው በከተማዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ሥርጭትን ለመግታት የሚሰሩ ሥራዎችን መቆጣጠርና መመሪያ መስጠታቸውን ይቀጥላሉ" ብሏል መግለጫው፡፡

      በአህጉሪቷ ክፉኛ በቫይረሱ ከተጠቁት መካከል ደቡብ አፍሪካ የቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።

      ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ በአገሪቷ ከተመዘገበው አጠቃላይ ቁጥር ግማሽ የሚሆን አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ መገኘታቸውን ተከትሎ ያገሬው ሰው በቁጥሩ ማሻቀብ እንዳይሸበር አሳስበዋል፡፡

      በአገሪቷ ትምህርት ቤቶች ቀስ በቀስ እየተከፈቱ ሲሆን የአምልኮ ሥፍራዎችም ቫይረሱን ለመግታት የሚያስችሉ መመሪያዎችን እንዲጠብቁ ሆነው ተከፍተዋል፡፡

    • በዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ ከተያዙ ነፍሰጡር ሴቶች ከግማሽ የሚበልጡት ጥቁሮችና ሌሎች ናቸው - ጥናት

      ነፍሰጡር ሴት በህክምና ክፍል

      በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል ከገቡ ነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል ከግማሽ የሚልቁት ጥቁሮች፣ እስያዊያን፣ ወይም ሌሎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ማህበረሰቦች መሆናቸውን አንድ አዲስ ጥናት አመለከተ፡፡

      በእንግሊዝ የህክምና ጆርናል ታትሞ የወጣው ይህ ጥናት፤ ከጎርጎሳውያኑ መጋቢት 1 እስከ ሚያዚያ 14 ባሉት ጊዜያት በዩኬ በሚገኙ 194 የህጻናትና እናቶች ጤና ክፍል ያገኛቸውን የታማሚዎች መረጃ ተመልክቷል፡፡

      በዚህም በተጠቀሰው ጊዜ ሆስፒታል ከነበሩ 427 ነፍሰጡር ሴቶች 233 ወይም 56 በመቶ የሚሆኑት ጥቁሮች፣ እስያዊያን ወይም ሌሎች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ማህበረሰቦች መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

      ከእነዚህም መካከል 103 የሚሆኑት እስያዊያን ሲሆኑ 90ዎቹ ጥቁሮች ናቸው፡፡

      የጥናቱ መሪ የሆኑትና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ኑፊልድ የህዝብ ጤና ክፍል ፕሮፌሰር ማሪያን ናይት፤ "የጥናቱ ውጤት ፈጣን የሆነ ምርመራ እና ማብራሪያ ይፈልጋል" ብለዋል፡፡

    • አምስት ሆስፒታሎች ህክምና የነፈጉት ህንዳዊ ሕይወቱ አለፈ

      ሆስፒታል

      በህንድ ኒውደልሂ የሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች ጋር ህክምና ማግኘት ያልቻለው የኮቪድ-19 ታማሚ 800 ኪሎ ሜትሮችን በባቡር አቆራርጦ ለህክምና ወደ ሆፓል ከተማ ያመራው ባሳለፍነው የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ነበር፡፡

      ይሁን እንጅ እሁድ ዕለት በሆፓል በሚገኝ ሆስፒታል እንዲገባ ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

      ይህንን ተከትሎ ባለሥልጣናት ከግለሰቡ ጋር በባቡር አብረው የተጓዙ ሰዎችን እየፈለጉ ነው፡፡ ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት እንደነበረው የተነገረው ይህ ግለሰብ እንዴት ባቡር ሊሳፈር እንደቻለም ባለሥልጣናቱን አሳስቧቸዋል፡፡

      የግለሰቡ የ18 ዓመት ልጅ እንደተናገረው እናቱም እሁድ ዕለት የባለቤቷን ሞት በተረዳችበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የአስም በሽታ አጋጥሟት ነበር ብሏል፡፡

      "ይህንኑ ለማሳወቅ ለደልሂ ሚኒስተር እና ጤና ሚኒስትር እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በትዊተርና ኢሜል መልዕክት ብልክላቸውም፤ ምላሽ አላገኘንም" ብሏል ልጁ፡፡

      በከተማዋ የሚኖሩ ሌሎች ነዋሪዎችም ከሆስፒታል እንዲመለሱ መደረጋቸውን በመግለጽ ተመሳሳይ ቅሬታ አስምተዋል፡፡

      የደልሂ መንግሥት ክፍት የሆኑ የሆስፒታል አልጋዎችን ለማወቅ የሚረዳው የስልክ መተግበሪያም ግራ አጋብቶናል ብለዋል፡፡

      መተግበሪያው በበርካታ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች ያልተያዙ አልጋዎች መኖራቸውን ቢያሳይም፤ ሆስፒታሎች ግን ምንም ቦታ አልነበራቸውም፡፡

      በህንድ ዋና መዲና ኒውደልሂ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 1ሺህ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡

      ይህም በመዲናዋ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 30 ሺህ ገደማ አድርሶታል፡፡

    • በናይጄሪያ ካልታወቁ 1 ሺህ ሞቶች 60 በመቶው ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ናቸው ተባለ

      አምቡላንስ ጎን የቆመ የጤና ባለሙያ

      የናይጄሪያ ጤና ሚኒስቴር ኦሳጌ ኢሃኒሬ፤ በሰሜናዊ ግዛት ካኖ ምክንያታቸው ካልታወቁ 1ሺህ ሞቶች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ከኮቪድ-19 ጋር ሳይያያዙ እንዳማይቀር አስታወቁ፡፡

      እዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰው በካኖ ግዛት ሚያዚያ እንዲሁም ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ባጋጠመውና አብዛኛው የቀደመ የጤና ችግር የነበረባቸው የእድሜ ባለጸጎች ሞት ላይ ጥናት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡

      እነዚህ ግለሰቦች አንዳንዶቹ በሆስፒታል ውስጥ ሆነው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ግን የሞቱት በቤታቸው ውስጥ ነው፡፡

      በሌሎች የናይጀሪያ ግዛቶችም ተመሳሳይ ነገር እያጋጠመ እንደሆነ ይነገራል፡፡

      በአፍሪካ ከፍተኛ ህዝብ ቁጥር ባላት ናይጄሪያ የሚደረገው ምርመራ አነስተኛ በመሆኑ ቫይረሱ ሳይታወቅ በህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት ሳይሰራጭ አይቀርም በሚል ባለሙያዎች ሰግተዋል፡፡

      በአገሪቷ እስካሁን 12 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 350 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

    • ኒውዚላንድ ያለገደብ መደበኛ እንቅስቃሴዋን ጀመረች

      ካፍቴሪያ

      የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ምንም እንኳን ገደቦች እየላሉ ቢሆንም አሁንም በአንዳንድ አገራት ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ ይስተዋላል፡፡

      ለኒውዚላንድ ግን ይህ ታሪክ የሆነ ይመስላል፡፡ የኒውዚላንድ ዜጎች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ አገራቸውን ያገኟት ከገደቦች ነጻ ሆና ነው፡፡

      በአገሪቷ አዲስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የለም፡፡ በመሆኑም በድንበር አካባቢ ከተጣሉት ገደቦች በስተቀር ወደ ቀደመው መደበኛ ሕይወቷ ተመልሳለች፡፡

      ኒውዚላንድ መጋቢት ወር መጨረሻ ገደማ ጥብቅ የሆነ ከቤት ያለመውጣት ገደብ ውስጥ የነበረች ቢሆንም ከ5 ሳምንታት በኋላ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመቀነሱ የተጣሉት እገዳዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡

      ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደም "ምን አልባት የሆነ ጊዜ አዲስ ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ" ሲሉ ሰዎች አሁንም ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አሳስበዋል፡፡

    • አሜሪካ በሁለት ወራት ውስጥ ዝቅተኛ የተባለውን የሞት ቁጥር መዘገበች

      የአስክሬን ሳጥን

      በአሜሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ 450 ሞት የመዘገበች ሲሆን ይህ ቁጥር በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የተመዘገበ ዝቅተኛው ቁጥር ነው ተብሏል፡፡

      በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት ግንባር ቀደም በሆነችው አሜሪካ፤ እስካሁን 110ሺህ 990 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን 2 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡

      ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአንድ ቀን ውስጥ ከ3ሺህ በላይ ደርሶ ነበር፡፡

      ነገር ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአገሪቷ በአንድ ቀን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአብዛኛው ከ1ሺህ በታች ወርዶ ታይቷል፡፡