በኢትዮጵያ 9 ሰዎች ሲሞቱ ተጨማሪ 409 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኘ

የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ባለባት ኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 933 ደርሷል። ከእነዚህም ውስጥ 5 ሺህ 645 አገግመዋል። አገሪቱ እስካሁን 197 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጥታለች። በኢትዯጵያ እስካሁን ድረስ 355 ሺህ በላይ ምርመራዎች መከናወናቸውን ከጤና ሚኒስቴርና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጫ የተገኘው መረጃ ያሳያል። በሕብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እየተስተዋለ በመሆኑ ሕዝቡ በሽታውን የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ ራሱንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ባለሙያዎች በየጊዜው እየመከሩ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ውሾች የኮሮናቫይረስን መለየት እንደሚችሉ በሙከራ ተረጋገጠ

    MDD

    ውሾች ኮሮናቫይረስን በሽታ መለየት እንደሚችሉ በሙከራ ተረጋገጠ።

    የጀርመን ተመራማሪዎች ኮሮናቫይረስን የሚያመጣውን ሳርስ-ኮቪድ-2ን በማሽተት የሚለዩ ውሻቸውን በማሰልጠን ውጤታማ መሆናቸውን አሳወቁ።

    ሃኖቨር ውስጥ በሚገኘው የእንስሳት ህክምና ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከጀርመን ሠራዊት ጋር በመሆን ለአንድ ሳምንት ውሾቹ በማሽተት ቫይረሱን እንዲለዩ በሰጧቸው ስልጠና ውጤታማ ሆነዋል።

    በተደረገው ስልጠናና ሙከራ ስምንት ውሾች ከቀረቡት ቫይረሱ ያለባቸው ናሙናዎች መካከል 94 በመቶ የሚሆኑትን በትክክል ለመለየት ችለዋል ተብሏል።

    አጥኚዎቹ እንዳሉት ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በስፖርት ውድድር ስፍራዎች ውሾቹን መጠቀም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ይረዳል።

    ከጀርመን በተጨማሪ ሌሎች አገራትም ቫይረሱን በሽታ ለመለየት ውሾችን ለመጠቀም ምርምርና ሙከራዎችን እያደረጉ ነው።

  2. ማያሚ ጭምብል በማያደርጉ ሰዎች ላይ የሚጣለውን ቅጣት ከፍ አደረገች

    የማያሚ ነዋሪዎች በጎዳና ላይ

    በቀን በአማካይ ከ2,500 በላይ ህሙማንን እያገኘች ያለችው የአሜሪካዋ ማያሚ ከተማ ከዚህ በፊት አውጥታው የነበረውን ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ጭምብል የማድረግ ደንብን በሚተላለፉ ሰዎች ላይ የሚጣለውን ቅጣት ከፍ አድርጋለች።

    ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ደንቡን ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ጊዜ ጥሰው የተገኙ ሰዎች የ100 ዶላር ቅጣት የሚጣልባቸው ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ጭምብል ሳያደርጉ የሚገኙ ሰዎች ደግሞ እስከ 500 ዶላር የገንዘብ ቅጣትና እስር ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

    ከዚህ ቀደም ጭምብል ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች በማስጠንቀቂያና ከፍተኛው 50ዶላር ቅጣት ይጣልባቸው ነበር።

    በመጋቢት ወር ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው የነበሩት የማያሚ ከንቲባ ፍራንሲስ ሱዋሬዝ እንዳሉት ደንቡን የሚያስፈጽሙ ፖሊሶች የሚሰማሩ ሲሆን፤ ከቅጣቱ የሚሰበሰበው ገንዘብ በበሽታው ምክንያት ችግር የገጠማቸውን አነስተኛ የንግድ ተቋማትን ለመደገፍ ይውላል።

    "ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ጭምብል ማድረግ ውጤታማ እንደሆነ ማስረጃዎች አሉ፤ ስለዚህም ሁሉም ነዋሪ ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርግ እንፈልጋለን” ሲሉ ከንቲባው ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

  3. ቻይናዊያን ጭምብል መጠቀምን በተመለከተ ትራምፕን እየተቹ ነው

    ትራምፕ

    የኮሮናቫይረስ መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቻይና ውስጥ በርካቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያደርጋሉ። በተቃራኒው አሜሪካ ውስጥ ጭምብል ማድረግ አወዛጋቢ እንደሆነ ቀጥሏል።

    በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጭምብል አድርገው የታዩት የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ በርካቶች ጭምብል አናደርግም ከሚሉት ጎራ ናቸው።

    በሌላ በኩል የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ጭምብል ማድረግ እንዲዘወተር የጤና ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

    አንድ የዋይት ሐውስ ሠራተኛ በኮቪድ-19 መያዙን ተከትሎ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው የሚል ሕግ ከዋሽንግተን ዲሲ ወጥቷል።

    ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ጭምብል አድገው የታዩ ዕለት በቻይናው ማኅበራዊ ሚዲያ ሲና ዊቡ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች መነጋገሪያ አድርገዋቸው ነበር።

    ትራምፕ ከሦስት ቀናት በፊት ጭምብል ማድረግ “ብሔራዊ ግዴታ ነው” ሲሉ ቻይናውያን ዜናውን መሳለቂያ አድርገውታል።

    ጭምብል የማያደርጉትን ትራምፕ፤ ጭምብል ከሚያደርጉት የቻይናው ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ጋርም እያነጻጸሩም ነው።

  4. በአፍሪካ ከ10 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል

  5. ለህጻናት ጭምብል አታድርጉ ተባለ

    ኢንግላንድ

    የኢንግሊዝ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ለህጻናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዳይደረግ አሳሰበ። ጭምብል ህጻናትን ሊያፍን ወይም ሊያንቅ ይችላል።

    በድረ ገጾች ላይ ለህጻናት የሚሆኑ ጭምብሎች እንደሚሸጡ ከታወቀ በኋላ ነው ተቋሙ መግለጫ የሰጠው።

    ከ11 ዓመት በታች ያሉ ልጆችን ሳይጨምር እንግሊዝ ውስጥ ሱፐርማርኬትና ሱቆች ውስጥ የአፍን የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ሆኗል።

    በተጨማሪም በተቋሙ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ቪቭ ቤኔት፤ ከሦስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ጭምብል ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

    “ጭምብል ህጻናቱን ሊያፍናቸውና ሊያንቃቸው ስለሚችል አይመከርም” ብለዋል።

  6. በኢትዮጵያ 9 ሰዎች ሲሞቱ ተጨማሪ 409 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኘ

    ቢቢሲ አማርኛ

    በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የ9 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ተጨማሪ 409 ሰዎች ላይ ደግሞ ቫይረሱ መገኘቱን የዕለተ ሐሙስ የወረርሽኙ ሪፖርት አመለከተ።

    ሪፖርቱ ጨምሮም 139 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን አመልክቷል።

    የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ሐምሌ 16/2012 ዓ.ም ባወጡት ዕለታዊ የኮሮናቫይረስ ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት በ6 ሺህ 898 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 409 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ኢትዮጵያ አስካሁን በአጠቃላይ በ357 ሺህ 058 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ያደረገች ሲሆን፤ 11 ሺህ 933ቱ ላይ ወረርሽኙ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    በተጨማሪም ከዚህ በፊት በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ተጨማሪ 139 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 5645 ሆኗል።

    እስካሁን በርካታ ህሙማን ከበሽታው በማገገማቸው በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 6 ሺህ 089 ሰዎች ሲሆኑ ከመካከላቸው የህክምና ክትትል ከሚደረግላቸው ሰዎች መካከል በጽኑ ታመው የሚገኙ 65 ሰዎች እንዳሉ ሪፖርቱ አመልክቷል።

    በቫይረሱ ምክንያት ተጨማሪ ዘጠኝ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በዚህም እስካሁን በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 197 ደርሷል።

  7. የኮሮናቫይረስ መድኃኒትን ከአፍሪካ ባሕላዊ መድኃኒቶች ለመፈለግ ቡድን ተቋቋመ

  8. በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አራት ሚሊዮን ተጠጋ

    አሜሪካ

    የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአሜሪካ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ወደ አራት ሚሊዮን ደርሰዋል። አሜሪካ በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ አገሮች ግንባር ቀደሟ ናት።

    በኮቪድ-19 ሳቢያ 143,000 ሰዎች ሞተዋል።

    የሮይተርስ አሀዝ በየሰዓቱ በአማካይ 2,600 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እንደሚመዘገብ ያሳያል።

    ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ያለው በኒው ዮርክ ውስጥ ሲሆን፤ ባለፉት ሳምንታት በሽታው በፍጥነት እየተሰራጨ ያለው ደግሞ በፍሎሪዳ እና በቴክሳስ ነው።

  9. በኢራቅ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ አለፈ

    ኢራቅ

    በኢራቅ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ከ100 ሺህ በላይ ሆኗል። የአገሪቱ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መረጃ መሠረት 4,122 ሰዎች አስካሁን ሕይወታቸው አልፏል።

    ሆኖም ግን ኢራቅ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከባግዳድ፣ ናጃፍ እና ባስራ ከተሞች ጀምራለች። ከነሐሴ በኋላ ሌሎች የአውሮፕላን ማረፊያዎችም ይከፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በረራዎች ላለፉት ጥቂት ወራት ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል።

    የኢራቅ ጎረቤት ኢራን በበሽታው ክፉኛ ከተጠቁ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች አንዷ ናት። በኢራን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ284,000 በላይ ሲሆኑ፤ 15,000 ሞት ተመዝግቧል።

  10. ኤምሬትስ ተሳፋሪዎቹ በኮቪድ-19 ከተያዙ የህክምና ወጪያቸውን እሸፍናለሁ አለ

    ኤምሬትስ

    ኤምሬትስ አየር መንገድ ተሳፋሪዎቼ ኮቪድ-19 ከያዛቸው የህክምና ወጪያቸውን እሸፍናለሁ በማለት የመጀመሪያው አየር መንገድ ሆኗል።

    የዱባዩ ኤምሬትስ ባወጣው መግለጫ፤ የኮቪድ-19 ህክምናንና ለለይቶ ማቆያ የሚወጣ ወጪን ይሸፍናል።

    ተሳፋሪዎቹ በቢዝነስ ክፍልም ይሁን በኢኮኖሚ ክፍል ቢበሩ የህክምና ወጪያቸው ይሸፈናል ተብሏል።

    አዲሱ የኤምሬትስ ደንብ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል። ተሳፋሪዎች በኮቪድ-19 ከተያዙ ለህክምና ወጪ የሚሆን 150,000 ዩሮ እና ለለይቶ ማቆያ ክፍያ በቀን 100 ዩሮ ተመድቧል።

    የኤምሬትስ ፕሬዘዳንት በዚህ ወር መባቻ ላይ በወረርሽኙ ሳቢያ ከ60 ሺህ ሠራተኞች 9 ሺህ የሚደርሱትን እንደሚቀንሱ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

  11. በቶክዮ በአንድ ቀን 366 ሰዎች ቫይረሱ ተገኘባቸው

    ቶክዮ

    ቶክዮ ውስጥ በአንድ ቀን 366 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው።

    የቶክዮ አገረ ገዢ ዩሪኮ ኮይኬ፤ ሰዎች ዛሬ የሚከበረውን ሕዝባዊ በዓል አስታከው ከቤታቸው እንዳይወጡ አሳስበዋል።

    ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ይገኛል። ይህም በምግብ ቤቶች፣ በምሽት ክለቦች እና በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከነበሩ ሰዎች የተገኘ ነው።

    ትናንት በመላው ጃፓን 795 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገልጿል።

  12. የሊቨርፑል ደጋፊዎች በአንፊልድ መሰብሰባቸውን ተከትሎ ዘጠኝ ሰዎች ታሰሩ

    የሊቨርፑል ደጋፊዎች
    የምስሉ መግለጫ, የሊቨርፑል ደጋፊዎች

    ዘጠኝ ግለሰቦች አካላዊ ርቀት የመጠበቅ ሕግን ተላልፈው፤ በሊቨርፑሉ አንፊልድ ስታድየም ዙርያ በመሰብሰባቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

    በሺህዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ደጋፊዎች ትላንት ምሽት በአንፊልድ ስታድየም ተሰብስበው ነበር።

    ቫይረሱ እንዳይሰራጭ በሚል ሰዎቹ እንዳይሰበሰቡ ለማድረግ ቢሞከርም እንዳልተቻለ ተዘግቧል።

    በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል መጠጥ በመጠጣትና ጸጥታ በማደፍረስ የተጠረጠሩ ይገኙበታል ተብሏል።

  13. ፖሊስ ከኮሮናቫይረስ በላይ ገዳይ የሆነባት አገር

  14. የተባበሩት መንግሥታት 'ለደሃ አገራት' ገንዘብ ይሰጥ እያለ ነው

    ኮሮናቫይረስ

    የተባበሩት መንግሥታት ደሃ ለሚባሉ አገራት ዜጎች ጊዜያዊ ደመወዝ ቢሰጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መግታት ይቻላል የሚል ሐሳብ አምጥቷል።

    የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም [ዩኤንዲፒ] ያወጣው ሃተታ እንደሚያሳየው የሚመደበው ገንዘብ በ132 አገራት ያሉ 2.7 ቢሊዮን የዓለማችን ሕዝቦችን ሊረዳ ይችላል።

    ገንዘቡ እያደጉ ያሉ ናቸው በተባሉ አገራት ያሉ ሰዎች ወረርሽኙ እስኪረጋጋ ድረስ ከቤት እንዳይወጡ ሊያግዝ ይችላል ተብሏል።

    ድርጅቱ ባወጣው ሃተታ ገንዘቡ ለአዳጊ አገራት ዜጎች በሦስት ዓይነት መንገድ ሊከፈል ይችላል የሚል መፍትሄ አምጥቷል።

    አንደኛው በወርሃዊ ደመወዛቸው ላይ ጭማሪ ማድረግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የኑሮ ሁኔታን መሠረት ያደረገ እርዳታ ነው። ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢና የኑሮ ሁኔታ መሠረት ሊሰጥ ይችላል የሚል አማራጭ ነው።

    የተባበሩት መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ድህነትን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል ሲል ያስጠነቅቃል።

    በመላው ዓለም በቫይረሱ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሲያዙ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።

  15. ደቡብ አፍሪካ በ24 ሰዓታት በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ አጣች

    ደቡብ አፍሪካ

    ደቡብ አፍሪካ በ24 ሰዓታት ብቻ 572 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ መሞታቸውን ይፋ አድርጋለች።

    ዕለተ ረቡዕ ይፋ የሆኑት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደቡብ አፍሪካ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 5940 ደርሷል።

    ከእነዚህ ሟቾች መካከል ግማሽ ያህሉ የተመዘገቡት በዌስተርን ኬፕ ግዛት ነው።

    ነገር ግን በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት ይፋ ያደረግችው የሃገሪቱ የፋይናንስ መናኸሪያ ተደርጋ የምትቆጠረው ጉዋቴንግ ግዛት ናት።

    ዌስተርን ኬፕ ግዛት ከጉዋቴንግ በመቀጠል ሁለተኛዋ በርካታ ሰዎች የተያዙባት ግዛት ናት።

    ደቡብ አፍሪካ እስካሁን ድረስ 394 ሺህ 948 ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙባት አረጋግጣለች።

  16. ብራዚል፡ በአንድ ቀን 67 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ

    ኮሮና ብራዚል

    ብራዚል በአንድ ቀን ከፍተኛ የሆነ የኮሮናቫይረስ ተያዦች ቁጥር አስመዝግባለች።

    ሃገሪቱ በአንድ ቀን ብቻ 67 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት አስታውቃለች።

    ከዚህም አልፎ የብራዚል ጤና ሚኒስቴር በአንድ ቀን ብቻ 13 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

    ወረርሽኙ ወደ ገጠራማ አካባቢዎች በመግባት የጤና አገልግሎት አቅርቦት የሌላቸውን ብራዚላውያን እያጠቃ መሆኑም ተነግሯል።

    ብራዚል እስካሁን ድረስ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት አረጋግጣለች። ከዩናይትድ ስቴትስ በመቀጠል ከዓለማችን በቫይረሱ በርካታ ሰዎች የተያዙባት ሃገር ናት።

    ከሁለቱ ሃገራት በመቀጠል ሕንድ፣ ሩስያና ደቡብ አፍሪካ ይከተላሉ።

  17. እንኳን ደህና መጣችሁ!

    covid-19

    ይህ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ተያያዥ ጉዳዮችን የምንዳስስበት የቀጠታ ዘገባ ገፃችን ነው።

    ዓለምን ሰቅዞ የያዘው የኮሮናቫይስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል። ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

    በተለይ ወጣቶች ምልክት የማያሳዩ ቫይረሱን ወደ አረጋውያን እንዳያስተላልፉ ስጋት አለ። ለዚህም ነው የጤና ባለሙያዎች ራሳችሁንና ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ከቫይረሱ ጠብቁ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉት። የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማጥለቅ ይመከራል።

    መልካም ቀን ይሁንላቹ!

  18. የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ከኮቪድ-19 እንዳላገገሙ በምርመራ ተረጋገጠ

    ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ

    የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ፣ ከሁለት ሳምንት በኋላም ሲመረመሩ ከኮሮናቫይረስ አለመዳናቸው ተረጋገጠ።

    ፕሬዝዳንቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

    ቦልሶናሮ ከዚህ በፊት ኮሮናቫይረስን አቃልለው የሚመለከቱ መሪ የነበሩ ሲሆን፤ ቢያዙ እንኳ እርሳቸው ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ "ስፖርተኛ ስለነበሩ" አነስተኛ መሆኑን ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው ይፋዊ መረጃ እንደሚያሳየው ፕሬዝዳንቱ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገላቸው ምርመራ ነፃ አለመሆናቸውን አመልክቷል።

    መግለጫው ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ "በጥሩ ጤንነት" ላይ እንደሚገኙ ጨምሮ አስታውቋል።

    ፕሬዝዳንቱ እሁድ ዕለት ከቤተመንግሥታቸው ውጪ ወጥተው የነበረ ሲሆን ደጋፊዎቻቸውንም በርቀት ሰላም ሲሉ ታይተዋል።

    ብራዚል በመላው ዓለም በቫይረሱ ከተጠቁ አገራት መካከል ሁለተኛዋ ስትሆን እስካሁን ድረስ 2.1 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ አረጋግጣለች።

  19. በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሺህ 500 በላይ ሆነ

    ቢቢሲ አማርኛ

    በኢትዮጵያ ተጨማሪ 452 ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱ ረቡዕ ይፋ የሆነ ሲሆን 8 ሰዎች ደግሞ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ማለፉ ተገለጿል።

    የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ሐምሌ 15/2012 ዓ.ም ባወጡት ዕለታዊ የኮሮናቫይረስ ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት በ7 ሺህ 294 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 452 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    የወረርሽኙ ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ከፍተኛው ቁጥር ማለትም 301ዱ የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ 34 ከጋምቤላ፣ 32 ከትግራይ፣ 21 ከአፋር፣ 19 ከኦሮሚያ፣ 12 ከሶማሊ፣ 17 ከደቡብና የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ከሌሎችም ክልሎች ናቸው።

    ዕለታዊው መግለጫ ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ተጨማሪ 58 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 5ሺህ 506 ደርሷል።

    በቫይረሱ ምክንያት ስምንት ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሰባቱ በአስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን በዚህም በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 188 ደርሷል።

    በኢትዮጵያ እስካሁን 350 ሺህ 160 ሰዎች ላይ ምርመራ የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ 11 ሺህ 524 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ ተረጋግጧል።

  20. በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ15 ሚሊዮን በላይ ሆነ

    በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሁናዊ መረጃ መሰረት በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ15 ሚሊየን በላይ ሆኗል።

    በአሁኑ ሰዓት በመላው ዓለም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15,000,424 መሆኑን የገለፀው ዩኒቨርስቲው የሟቾች ቁጥር ደግሞ 617, 832 እንደደረሰ የአሁናዊ መረጃው ላይ አስፍሯል።

    እንደ ዩኒቨርስቲው መረጃ ከሆነ በዓለም ላይ ከፍተኛው የቫይረሱ ስርጭት የታየባቸው የዓለማችን አገራት አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ፔሩ ናቸው።

    ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባቸው አገራት ደግሞ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እና ሜክሲኮ መሆናቸው ተጠቅሷል።

    የዩኒቨርስቲው መረጃ የተጠናቀረው ከ188 አገራት በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ነው።