የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አገራቸው በየመን የሚካሄደውን ግጭት በውይይት ለመፍታት የሚቻሉትን አማራጮች ሁሉ መሞከር እንደምትፈልግ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የግብፅ ጦር በኢራን ድጋፍ ከሚንቀሳቀሱት ሁቲዎች ጋር በሚደረገው ጦርነት
ሳዑዲ አረቢያን ለመደገፍ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይፓርላማው በሚቀጥለው ሳምንት ድምፅ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ነው።
በቀጣናው ካሉት ትላልቅ ኃይሎች አንዱ የሆነው የግብፅ ጦር በቀጥታ በዚህ ግጭት ውስጥ መሳተፉ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በሁቲዎች መካከል ያለውን ውጥረት በእጅጉ ያባብሰዋል።
ይህ ግጭት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ እያካሄዱት ባለው እና እየተስፋፋ በመጣው ጦርነት ውስጥ አለመረጋጋትን ይበልጥ እያባባሰ መጥቷል።
ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት ለሳዑዲ አረቢያ የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማጽደቅ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀዋል።
እሁድ ዕለት ዝግ ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ፣ የፓርላማ አባላቱ ለውይይት ተጨማሪ ጊዜ እንዲኖር በማሰብ ድምፅ የመስጠት ሂደቱን እስከ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ድረስ አራዝመውታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ እና የስለላ አገልግሎት ኃላፊው ሀሰን ራሻድ ረቡዕ ዕለት ወደ ሪያድ ተጉዘው ከፕሬዚዳንት ሲሲ የተላከ ደብዳቤ ለሳዑዲ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን አድርሰዋል።
ፕሬዚዳንት ሲሲ እንደገለጹት፣ ግብፅ የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ የሳዑዲ አረቢያን ግዛትና ድንበሮችን መከላከል ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑን ገልጸው የመን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዕቅድ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ግብፅ የምትሰጠው ድጋፍ ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም።
አብደላቲ ሐሙስ ዕለት ግብፅ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመድረስ የሚቻሉትን መንገዶች በሙሉ ለመፈተሽ ትፈልጋለች ብለዋል።
በተጨማሪም ግብፅ፣ ሁቲዎች በመስከረም ወር በባብ አል-ማንደብ ወሽመጥ አቅራቢያ ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ትፈልጋለች።
ይህ ወሽመጥ ወደ ቀይ ባህር መግቢያ ላይ የሚገኝ ወሳኝ የመርከብ መስመር ሲሆን፣ ወደ ግብፅ የስዊዝ ካናል የሚያደርስም ቁልፍ መተላለፊያ ነው።
አብደላቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሳዑዲ አረቢያ የምታደርገውን ጥረት እየደገፈች በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካዊ መፍትሄን መከተል እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
በየመን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን መንግሥት የሚደግፈው እና በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምረት ከሁቲ ታጣቂዎች
ጋር የሚያደርገው ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።
ሁቲዎች ወደ ባብ አል-ማንደብ ወሽመጥ መጠጋታቸው በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።
ከዚያ ወዲህም ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን እና የነዳጅ ተቋማትን አጥቅቷል።
በዓለም ቀዳሚ የነዳጅ ላኪ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ፣ ለግብፅ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አጋር ነች።
በየመን ውስጥ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሁቲዎች ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ከሰሜናዊው ዋና ከተማ ሲያስወጡ ነው።
ይህም በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን አስከትሏል።