የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ለትራምፕ በሚሰጡት ሽፋን ዙሪያ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እየመረመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር በቅርቡ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጊዜያዊነት የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን መስጠት አቋርጠው በነበሩ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ የፌዴራል የውድድር ሕጎችን ጥሰው እንደሆነ የማጣራት ምርመራ መጀመሩን ገለፀ።
ባለፈው ወር የትራምፕ አስተዳደር የሲኤንኤን፣ ኤምኤስ ናው እና የፖሊቲኮ ጋዜጠኞችን የዋይት ሀውስ መግቢያ ፈቃድ መሰረዙን ተከትሎ አምስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለፕሬዝዳንቱ የሚሰጡትን ሽፋን ለብዙ ቀናት አቋርጠው ነበር።
ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ኤቢሲ፣ ሲቢኤስ፣ ሲኤንኤን፣ ኤንቢሲ እና ፎክስ ኒውስ ከዋይት ሀውስ የጋዜጠኞች ቡድናቸው ጋር በተያያዘ የተደረጉ ግንኙነቶችን የሚያሳዩ መረጃዎቻቸውን እንዲያስረክቡት ጠይቋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ለፕሬዝደንቱ መግለጫዎች ሽፋን ላለመስጠት ያሳለፉት ውሳኔ፣ ኩባንያዎች በፀረ-ውድድር አሠራር እንዳይሳተፉ የሚከለክለውን የሸርማን ሕግ ሊጥስ እንደሚችል ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የፕሬስፑል (የጋዜጠኞች ቡድን) አባላት የሚሰበስቡትን መረጃ እና ምሥሎች በመደበኛነት ቡድኑን ላዋቀሩ የዜና ተቋማት ያጋራሉ።
የፍትሕ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ፣ የሚመለከተው የመሥሪያ ቤቱ ክፍል “እነዚህ የዜና ተቋማት በጋራ ባሳለፉት ውሳኔ የውድድር ሕጎችን ጥሰዋል ወይስ አልጣሱም የሚለውን ለማረጋገጥ ምርመራ እያካሄደ ነው” ብለዋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
ትራምፕ ባለፈው ወር ሲኤንኤን፣ኤምኤስ ናው እና ፖሊቲኮን “ልብ ወለድ ወይም ውሸት” የሚጽፉ ናቸው በማለት ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ መከልከላቸው ይታወሳል።
በኋላ ላይ ግን በዳኛ ውሳኔ ፈቃዳቸው ተመልሶላቸዋል።




















