ልጇን የላቀ ዩኒቨርስቲ ለማስገባት ግማሽ ሚሊዮን ብር ጉቦ የከፈለችው ተዋናይት ጥፋተኝነቷን አመነች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በደስፐሬት ሀውስ ዋይቭስ ፊልም የምትታወቀው አሜሪካዊቷ ተዋናይት ልጆቻቸውን በላቁ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለማስገባት በማጭበርበር ቅሌት ዝርዝር ውስጥ መካተቷን ተከትሎ ጥፋተኛ እንደሆነች አምናለች።
ልጇን የመካድ ስሜት እንደተሰማትና ባጠፋችው ጥፋትም እንዳፈረች ገልፃለች።
በጎርጎሳውያኑ 2017 የልጇን ፈተና እንዲስተካከል 15ሺ ዶላር ከፍላለች ተብሏል።
ከ56 አመቷ ተዋናይት በተጨማሪ ጥፋተኛ ከተባሉት አምሳ ግለሰቦችም መካከል 14ቱ ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል፤ ከነዚህም ውስጥ የኮሌጅ አትሌቲክስ አሰልጣኞች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ተዋናይቷ በሰጠችው መግለጫ " መሉ በሙሉ ጥፋተኛ መሆኔን ከከፍተኛ ፀፀትና እፍረት ጋር እቀበላለሁ። ለፈፀምኩትም ድርጊት ኃላፊነቱን ለመውሰድና ያስከተለውን ውጤት እቀበላለሁ" ብላለች።
አክላም " በልጄ፣ በቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና የስራ ባልደረቦቼና ህመምና መሸማቀቅ አድርሻለሁ" ብላለች።
"እነሱን ከልቤ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ በተለይም ኮሌጅ ለመግባት ቀን ተሌት ለሚያጠኑና ለሚታትሩ ተማሪዎችና እንዲሁም ልጆቻቸውን በትምህርት ለመደገፍ ብዙ መስዋዕትነትን ለከፈሉ ወላጆች" ብላለች።
ስለ ጉዳዩ ልጇ ምንም እንደማታውቅም በመግለጫዋ ጨምራ ገልፃለች።
የአሜሪካው የወንጀል ምርመራ ድርጅት ኤፍቢአይ "ኦፐሬሽን ቫርስቲ ብሉስ" ብሎ በሰጠው ኦፐሬሽን እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2011-2018 ድረስ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በምዝገባ ስርአቱ የተፈፀሙ ማጭበርሮችን አጥንቷል።
እንደ ምርመራው ውጤት ከሆነ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለማስገባት ጉቦ ከመክፈል በተጨማሪ፤ ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ውስጥ በስፖርት ቡድኖች አባል እንደሆኑ ተደርጎ በፎቶ ሾፕ ሐሰተኛ ፎቶዎች ወጥተዋል።
ከነዚህ ውስጥ ፌሊሲቲ ሀፍማንና ሌላ ታዋቂ የሆሊውድ ተዋናይት ሎሪ ሎግሊን ከታዋቂዎቹ መካከል ሲሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የስራ አስፈፃሚዎችም አሉበት ተብሏል።
ሎሪ ሎግሊና ባለቤቷ ሁለት ልጆቻቸውን በሳውዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ለማስገባት 500ሺ ዶላር ጉቦ ከፍለዋል ተብሏል።
ሎሊ ሎግሊና እንደሌሎቹ ራሳቸውን በጥፋተኝነት ያላጋለጡ ሲሆን፤ ወንጀሉንም አስመልክቶ ይፋዊ መግለጫ እንዳልሰጡ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
































