የ26 ዓመቱ ሞዴል መድረክ ላይ ራሱን ስቶ ሞተ

ታለስ ራሱን ስቶ ከመውደቁ ከደቂቃዎች በፊት
የምስሉ መግለጫ, ታለስ ራሱን ስቶ ከመውደቁ ከደቂቃዎች በፊት
ታትሟል

ታዋቂው ብራዚላዊ ሞዴል ታለስ ሱአረስ በሳኦፖሎ የፋሽን ሳምንት መድረክ ላይ አድርጓቸው የነበሩትን አልባሳት ለማሳየት መድረክ ላይ ወጥቶ ጫፍ ድረስ ከተራመደ በኋላ በመመለስ ላይ ሳለ ራሱን ስቶ ይወድቃል። መጀመሪያ ላይ ብዙዎች ነገሩ የትርኢቱ አካል እንጂ ድንገተኛ አደጋ አልመሰላቸውም ነበር።

ለድንገተኛ አደጋዎች በመድረኩ የተገኙ የነፍሰ አድን ሰራተኞች ወደ መድረኩ ሮጠው ሞዴሉን ከመድረኩ አፋፍሰው ለማንሳት ሲሞክሩ ነው ብዙዎች ነገሩ ትርኢት እንዳልሆነ የገባቸው።

ወዲያው አብረውት መድክ ላይ የነበሩ ሌሎች ሞዴሎች እንዲሁም ታዳሚዎች በከባድ ድንጋጤ ተዋጡ።

ሞዴልና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት አክቲቪስት የነበረው ታለስ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም። የመድረኩ አዘጋጆች የታለስን ሞት በትዊተር ገፃቸው ይፋ ቢያደርጉም ስለ አሟሟቱ ያሉት ዝርዝር ነገር ግን የለም።

ለቤተሰቦቹ መፅናናትን በመመኘት በዚህ ከባድ ጊዜ ለቤተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አሳውቀዋል።

ከህልፈቱ ከሰዓታት በፊት ታለስ ስለ ሳኦ ፖሎ የፋሽን ዥግጅት ኢንስታግራም ገፁ ላይ ፎቶ ለጥፎ ነበር። ኋላ ላይ መድረክ ላይ እንዴት ራሱን ስቶ እንደወደቀ የሚያሳየው ቪዲዮም በማህበራዊ ሚዲያ ሲሽከረከር ነበር።