በሊቢያ የአማፅያኑ መሪ በረመዳን ወቅት የጥቃት ዘመቻዬን አጠናክረዋለው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በምስራቃዊ ሊቢያ በኩል ዋና ከተማዋን ትሪፖሊን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሚሊሻ ዋና አዛዥ ካሊፋ ሃፍታር የተባበሩት መንግስታት የጠየቀውን የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ጎን በማለት በረመዳን ጾም ወቅት ወታደሮቹ ከፍተኛ የማጥቃት ዘመቻ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት የቅዱሱን የረመዳን ወር በማስመልከት ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ጀነራል ካሊፋ ግን አለመስማማታቸውን ገልጸዋል።
ጀነራሉ አክለውም ወታደሮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በዚህ ከባድ ወቅት ጥንካሬና ቁርጠኝነት ማሳየት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር የሊቢያ ብሄራዊ ግንባርን የሚመሩ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈውን መንግስት ጠራርጎ በማስወጣት ዋና ከተማዋ ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል።
ከአንድ ወር በፊት ትሪፖሊን ለመያዝ የሚደረገው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደደዱ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይታቸው እንዳለፈ ተዘግቧል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ በጀነራል ሃፍታር ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸው ሲዘገብ አይ ኤስ የተባለው እስላማዊ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።
የጀነራል ሃፍታር ወታደሮች ባሳለፍነው ጥር ወር በነዳጅ ምርት የሚታወቀውን ደቡባዊ ክፍል መቆጣጠራቸው የሚታወስ ነው።
አይ ኤስ በበይነመረብ ባስተላለፈው መልዕክት ሳብሃ በተባለችው አካባቢ በጀነራሉ ማሰልጠኛ ካምፕ ላይ በወሰደው እርምጃ 16 ሰዎች መገደላቸውን ያስታቀ ሲሆን በእስር ላይ የነበሩ የቡድኔ አባላትንም ነጻ አውጥቻለው ብሏል።
































