ኮሮናቫይረስ በጋና፡ የኦንላይን የቀብር ሥነ ስርዓት እና ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጋና ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ያለውን የቀብር ሥነ ሥርዓት እና ምርጫን በተመለከተ ስላለው አዲስ ልማድ ጋዜጠኛና የቀድሞዋ የጋና የመንግሥት ሚኒስተር ኤልሳቤት ኦሄኔ የሚከተለውን ለቢቢሲ ጽፈዋል።
"ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ሕይወት ከተለመደው ተለዋውጧል።
ልክ እንደመተቃቀፍና መጨባበጥ ይቀራል ብሎ ማንም ሰው አልሞት እንደማያውቀው ሁሉ ወረርሽኙን ለመታገል ስንል ብዙ እየተማርን ነው፡፡
አካላዊ መራራቅ፣ ራስን ማግለል እና ለይቶ ማቆያ በየእለቱ የምንጠቀማቸው ቃላት ሆነዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ያህል ምግብ እንደሚመገቡ ማወቅ ጀምረዋል፡፡
በጋና በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 16 ቢሆንም ከመናገር የምንቆጠባቸው ነገሮች መጥተዋል- መቃብር ቦታዎች ሞልተዋል የሚል፡፡
የቀብር ሥነ ስርዓት ለመፈጸም መሰባሰብ ተክልክሏል፡፡ በመሆኑም በተለመደው መልኩ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ የሚወዱትን ሰው አልቅሶ መሸኘት ቀርቷል፡፡
በግል የቀብር ሥነ ስርዓት መፈጸም ቢቻልም ከ25 በላይ ሰዎች መገኘት አይችሉም፡፡ ይህ ደግሞ ለጋናዊያን የማይታገሱት ልማድ ሆኗል፡፡
በመሆኑም ይህ አስከፊ በሽታ ይጠፋል በሚል ተስፋ እና ለሟቾቹ በተከበረ መልኩ የቀብር ሥርዓት ለመፈጸም የሞቱ ሰዎችን አስክሬን በመቃብር ቤቶች ማስቀመጣችንን ቀጥለናል፡፡
በአዲሱ ውሳኔ መሰረት በጋና የቀብር ሥነ ስርዓት በቴክኖሎጅ የተደገፈ ሆኗል፡፡
የቀብር ሥነ ስርዓቱ ቁጥራቸው 25 ወይም ከዚያ በታች የሚገኙ ሲሆን፤ ሥነ ስርዓቱ ግን በቀጥታ በኦንላይን ሥርጭት ይተላለፋል፡፡ በመሆኑም በርካታ ሰዎች ቤታቸው ተቀምጠው በላፕቶፓቸው ሥነ ስርዓቱን ይካፈላሉ፡፡
ይህ ልምድ በዚሁ ከቀጠለ የቀብር ሥነ ስርዓት አፈጻጸማችን ሁኔታ ይቀየራል፡፡ እኔ ባለፈው ሳምንት በኢንተርኔት አማካኝነት የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ጅንስና ቲሸርት ለብሼ፤ ማንም ሰው በእንዲህ ዓይነት አለባበስ መልኩ ቀብር ሥነ ስርዓት ላይ አይገኝም፡፡
የፋሲካ በዓል የተከበረበትን እሁድ ጨምሮ ሰባት እሁዶችን ቤተ ክርስቲያን ሳንሄድ አሳልፈናል፡፡ ኮሮናቫይረስ ለሁላችንም አስፈሪ ከመሆኑም በላይ ድራማ ይመስላል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በቅዱስ ረመዳን ወር ላይ እንገኛለን፡፡ ሙስሊሞች ያለ ሕብረት ጸሎት ጾም ጀምረዋል፡፡ ከማፍጠሪያ በፊት ወደ መስጊድ በመሄድ የሚያደርጉት የሕብረት አምልኮም ቀርቷል፡፡ ባልተረጋጋ ጊዜ ውስጥ ስላለን አብዛኞቻችን ይህንን ተቀብለነዋል፡፡
የጋና መዲና አክራ እና አካባቢዋ እንዲሁም ሁለተኛ ከተማዋ ኩማሲ ለሦስት ሳምንታት ያህል በእንቅስቃሴ ገድብ ውስጥ ነበሩ፡፡ አሁን እንኳን ሰዎች መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡"
ምርጫ
በሚመጣው የፈርንጆቹ ታህሳስ ወር የፕሬዚደንትና የፓርላማ ምርጫ ይካሄዳል፡፡
እዚህ ምርጫ ሲካሄድ ብዙ ጊዜ ግጭቶች ይፈጥራሉ፡፡ የምርጫ ዘመቻዎችም የደመቁና የተጨናነቁ ናቸው፡፡ ታዲያ ብጥብጥ እንዳይፈጠር እድል ላለመስጠት ዝግጅቱ የተካሄደው በጣም በተጨናናቀ የጊዜ ሰሌዳ ነው፡፡
ከዚያ ቫይረሱ ገባ፤ ቫይረሱ የመጀመሪያውን ተግዳሮት የጣለው በብሔራው ምዝገባ ባለስልጣን ላይ ነው፡፡ ለምርጫው መጀመሪያ የሚደረገው መታወቂያ መስጠት ነበር፡፡ በቫይረሱ ምክንያት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከ16 ዓመት በላይ ላሉት መታወቂያ ሰጥቶ መጨረስ አልቻለም፡፡
የምርጫ ቦርድ ደግሞ አዲስ መራጮችን ምዝገባ ማጠናቀር ይፈልጋል፤ ይሁን እንጅ ተቃዋሚው የብሔራዊ ዲሞክራቲክ ኮንግረስ ፓርቲ ምንም አልመዘገበም፡፡ በርግጥ ኮሚሽኑ ምዝገባ ሂደቱን ከሳምንት በፊት ለማጠናቀቅ እቅድ ቢኖረውም የሰዎች መሰባሰብ በመከልከሉ ባለበት ቆሟል፡፡
በዚህ ምርጫ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሶስተኛ ጊዜ የሚፋጠጡበት ነው፡፡
የምርጫ ዘመቻዎችን እንዴት ማካሄድ እንደሚቻልም ግራ ያጋባ ጉዳይ ሆኗል፤ ለፓርቲዎች ክርክርም ፍላጎቱም እምብዛም ነው፡፡
የአገሪቷ ፕሬዚደንት ናና አኩፎ አዶ ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ እስካሁን ስምንት ጊዜ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ሕዝቡም ንግግራቸውን ተቀብሏል፡፡
ካደረጓቸው ንግግሮች መነጋጋሪያ የነበረው "ኢኮኖሚያችንን እንዴት እንደምናንሰራራው እናውቃለን፤ የማናውቀው ሰዎችን ወደ ሕይወት እንዴት መመለስ እንደምንችል ነው " የሚለው ነበር፡፡
ፕሬዚደንቱ "ቫይረሱ ፖለቲካዊ ቀለም የለውም፤ ፖለቲካዊ ለማድረግም ጊዜው አሁን አይደለም፤ የጋራ ጠላታችንን መታገል አለብን" ብለዋል፡፡
































