የዶናልድ ትራምፕ የበኩር ልጅ "ገንዘብ እያባከነ ነው" ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዶናልድ ትራምፕ የበኩር ልጅ ባለፈው ዓመት ወደ ሞንጎሊያ ለአደን ሄዶ ነበር። ብቻውን አይደለም ታዲያ፣ የትራምፕ የልጅ ልጅን ጨምሮ አጀቡ ብዙ ነው።
ይህ የትራምፕ የበኩር ልጅ አንድ የዱር እንሰሳ ለማደን ታዲያ ወደ 75ሺህ ዶላር ነው የከሰከሰው።
ዶናልድ ትራምፕ ጁንየር ተኩሶ የገደለው እንሰሳ ብርቅዬ የሚባል ነው። ከምድረ ገጽ ይጠፋል በሚል የሚፈራለትና በስስት የሚታይ ነው። ሆኖም አድኖታል።
እንዴት ይህን እንሰሳ ለማደን ፍቃድ አገኘ የሚለው የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኖ ልጁ ሽርሽር ባማረው ቁጥር ከአሜሪካ መንግሥት ካዝና የሚወጣው ወጪ ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ እየተነሳበት ነው።
በአሜሪካ ሕግ ፕሬዝዳንቱና የፕሬዝዳንቱ ቤተሰብ ልዩ ጥበቃና ከለላን ያገኛል። ይህን በሚያከናውነው ክፍል ስር ታዲያ እንዲህ ዓይነት ተያያዥ ወጪዎችም ይሸፈናሉ።
ይህ የትራምፕ የበኩር ልጅ ሐሴት ለማድረግ ለአደን በወጣ ቁጥር የሚወጣው ወጪ ታዲያ ለፕሬዝዳንቱ ከሚደረገው የልዩ ጥበቃ ወጪ ጋር አብሮ የሚወራረድ ነው።
ነገሩን ያጠኑ ሰዎች እንደሚሉት የትራምፕ ቤተሰብ እንዲህ አይነት ቅንጡ ጉዞ በማድረግ የኦባማ ቤተሰብን በ12 እጥፍ ይበልጣል።
የኦባማ ቤተሰብ በዚህ ዓይነት እጅግ ወጪ ቆጣቢ እንደነበሩ ነው እየተነገረ ያለው።
የትራምፕ ቤተሰብ ቅንጡ የሕይወት ዘይቤ ግን የልዩ ጥበቃ በጀትን እየመጠጠ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።
የዶናልድ ቤተሰብ በአማካይ በዓመት አንድ ሺህ የውጭ ጉዞ ያደርጋሉ። የኦባማ ቤተሰብ ያደረገው የመዝናኛ ጉዞ ግን ከዚህ በብዙ እጥፍ ያነሰ ነበር።
እንዲህ ዓይነት ወጪዎችን እግር በእግር እየተከታተለ የሚያጠና አንድ ድርጅት የቡድን መሪ ባወጡት ዘገባ እንዳስታወቁት፤ የዶናልድ ትራምፕ ቤተሰብ የአሜሪካ ግብር ከፋዮችን አንጡራ ሀብት እየመጠጠ ነው፤ ለዚህ ማሳያም የበኩር ልጃቸው ብቻ ለአንድ አደን ያወጣው 75 ሺህ ዶላር ነው ብለዋል።
አንድ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ የዶናልድ ትራምፕ የበኩር ልጅ ጉዳይ አስፈጻሚ ለሲኤንኤን እንደገለጸው ግን የዚህ ባለፈው ነሐሴ ወር የተደረገው ሽርሽር ወጪ በቤተሰቡ የተሸፈነ እንጂ ከአሜሪካ ልዩ የጥበቃ ኃይል ጋር የሚያያዘው ነገር የለም። ከልዩ ጥበቃው ጋር የሚያያዘው ወጪ አደኑ ሳይሆን ለጥበቃ የወጡ ወጪዎች ብቻ ናቸው።
የዶናልድ ትራምፕ የበኩር ልጅ የዚህን የሲክሬት ሰርቪስ ልዩ ጥበቃ ከለላ ማግኘት እንደ ፕሬዝዳንቱ ግድ ባይለውም ከፈለገ ግን መብቱ ተደርጎ ይታዘዝለታል።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ በመሆኑ የልዩ ጥበቃ ከለላ የማግኘት ሙሉ መብት ያለውም ለዚሁ ነው።
ያም ሆኖ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ለዚህ ልጅ ቅንጡ ሕይወት ምን ያህል ዋጋ እየከፈለ ስለመሆኑ የማወቅ መብት አለው ይላሉ የጥናት ቡድኑ መሪ።
ሌላ ጥናት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ይህ የዶናልድ ትራምፕ የበኩር ልጅ በሞንጎሊያ የሚገኝ ብርቅዬ እንሰሳ ለማደን ከሞንጎሊያ መንግሥት ፍቃድ ያገኘው በእጅ አዙር ነው።
ይህን የዶናልድን ልጅ የአደን ችሎታ ለማድመቅ ለሪፐብሊካን ፓርቲ በመለገስ የሚታወቁ አንድ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሀብትም አብረውት ነበሩ። የባለሀብቱ ወጪ የተሸፈነው በራሳቸው ይሆን ወይስ በልዩ ጥበቃ ቢሮ የታወቀ ነገር የለም።
የትራምፕ ልጅ እያደናቸው ያሉት አርጋሊ በሚል የሚታወቁት የበግ ዝርያዎች በዓለም ላይ ብርቅዬና ዘራቸው እንዳይጠፋ የሚፈራላቸው እንሰሳት ናቸው።
ይህ የትራምፕ ልጅ ታዲያ ለአደን ሞንጎሊያ በሄደበት የአገሪቱን ፕሬዘዳንት ከልማጊን ባቱልጋን ጭምር አግኘቷቸዋል። እኚህ ፕሬዝዳንት የትራምፕ ልጅ ካገኛቸው በኋላ ነገሮች መልክ ያዙላቸው መሰል በወሩ አሜሪካንን ጎብኝተው ፕሬዝዳንት ትራምፕን አግኝተዋቸዋል።
የትራምፕ ልጅ በአመዛኙ ጊዜውን የሚያሳልፈው በመዝናናት ሲሆን ይህን ቅንጡ ሽርሽሩን የሚያሳዩ ፎቶዎችን በተከታታይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራል።
እርሱና ቤተሰቡ ምን ያህል እየተዝናኑ ስለመሆኑ እና ሞንጎሊያ ስላላት አስደናቂ የመዝናኛ ተፈጥሮ ጸጋ በሞንጎሊያ ፈረሶች ላይ ተፈናጦ የሚያሳዩ ምስሎቹን በማኅበራዊ መዲያ ሲያጋራ ነበር የሰነበተው።
ትራምፕ ጁንየር እንደ እህቱ ኢቫንካ ትራምፕ በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ በኃላፊነት አልተሾመም። ይፋ የሆነ ሥልጣንም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የለውም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚያጋራቸው ቅንጡ የመዝናኛና የአደን ወጪዎቹ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል።
የትራምፕ የኩር ልጅ መሣሪያ የመታጠቅ መብትን በአሜሪካ ምድር እንዲከበር የሚሟገት ሰው ነው።
































