የትግራይ ምርጫ፡ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል
![ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነር [ከቀኝ ወደ ግራ የመጀመሪያው]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/CB0A/production/_114187915__114185412_5fbcfc94-f61d-4026-b488-771d17a2e46f.jpg.webp)
ታትሟል
በትግራይ ክልል ለሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገባቸው ተነገረ።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተካሄደው የትግራይ መራጮች ምዝገባ 2,740,888 ሰዎች መመዝገባቸውን የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽነር አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት መመዝገብ ያልቻሉ ሰዎች ቅዳሜ እና እሑድ እንዲመዘገቡ የተደረገ ሲሆን፤ አሁን የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የምርጫ ቅስቀሳው ደግሞ አርብ ይገባደዳል ተብሏል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ እስካሁን ሦስት የምርጫ ክርክሮች ተካሂደዋል። የመጨረሻው ክርክር ደግሞ በቀጣዩ ሐሙስ ይከናወናል።
ምርጫውን ለማስፈጸም አስፈላጊ ግብዓቶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አቶ ሙሉወርቅ ተናግረዋል። 29 ሺህ 600 የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ቅሬታ ሰሚዎች እና ታዛቢዎች እንደተዘጋጁም አክለዋል።
በተጨማሪም ምርጫውን ለመታዘብ ከውጪ የሚመጡ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በተቋቋመው ግብረ ኃይል በኩል እንደሚያልፉ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
በትግራይ ክልል 2,672 የምርጫ ጣቢያዎች አለ።
በክልላዊው ምርጫ አምስት ፓርቲዎችና አራት የግል ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ምርጫው የሚከናወነው ጷግሜ 4 ቀን 2012 ዓ. ም. ነው።



































