"ትራምፕ አጭበርባሪ፣ ሞላጫ፣ ውሸታም ዘረኛ፣ አታላይ፣ እና ሴት አሳዳጅ ነው" የፕሬዝዳንቱ የቀድሞ ጠበቃ

ዶናልድ ትራምፕና የቀድሞው ጠበቃ ማይክል ኮኸን
ታትሟል

የዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ የግል ጠበቃ ማይክል ኮሐን አዲስ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ዲስሎያል ይሰኛል፡፡ ጠበቃው ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ ዋሽተኸል፣ ያልተገባ ክፍያ ፈጽመኸል በሚል ነበር ዘብጥያ የወረደው፡፡

መጽሐፉን ጽፎ የጨረሰውም እዚያው እስር ቤት በነበረበት ወቅት ነው፡፡

በዚህ አነጋጋሪ መጽሐፉ ታዲያ ፕሬዝዳንቱን በቅርብ እንደሚያወቁ ጮማ መረጃዎችን አውጥቷል፡፡

ትራምፕ ‹ልክ እንደ ሰፈር ዱርዬ ነው ባህሪው› የሚለው ጠበቃ ኮውን ጥቁሮችን በተመለከተ ከፍተኛ ንቀት ነበረበት ይላል፡፡

የዚህን መጽሐፍ መታተም ተከትሎ የዋይትሐውስ ፕሬስ ኃላፊዋ ካይሌ ማካኔኒ በሰጠችው መግለጫ ኮሀንንን ሞልጫዋለች፡፡

‹‹ይህ አሳፋሪና ወራዳ ጠበቃ ነበር፡፡ ለኮንግረስ ውሸት የተናገረ ጠበቃ ነው፡፡ ምንም የሚታመን ሰው አይደለም፡፡ ስለዚህ ዶናልድን ለማጠልሸት የጻፈው ነገር በጭራሽ ተቀባይነት የለውም›› ብላለች፡፡

ጠበቃ ማይክል ኮውን በመጽሐፉ እሱ ለታሰረበት ጉዳይ ትራምፕ ጥፋተኛ እንደሆኑ የጠቀሰ ሲሆን የድሮ አለቃውን ‹‹አጭበርባሪ፣ ሞላጫ፣ ውሸታም፣ ዘረኛ፣ አታላይ፣ ሴት አሳዳጅ›› ነበር ብሏል፡፡

ማክሰኞ ዕለት ለገበያ የዋለው ‹ዲስሎያል› መጽሐፍ ከያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

1.ጥቁሮችን በተመለከተ

ትራምፕ በጅምላ ጥቁሮችን ይንቃሉ፡፡ በፖለቲካም፣ በሙዚቃም፣ በባሕልም ይላል ጠበቃ ማይክል ኮሐን፡፡ ይህ ትራምፕ ለጥቁሮች ያላቸው ንቀት ታላቁን የፀረ አፓርታይድ መሪ ኔልሰን ማንዴላንም ይጨምራል፡፡

ጠበቃ ኮሐን ለዚህ ማስረጃ ብሎ ያቀረበውና ትራምፕ በአንድ ወቅት ተናገሩት ያለውን ነው፡፡

‹‹እስኪ በጥቁር የምትመራ አንድ አገር፣ አንድ የጥቁር አገር፣ አንድ ቆሻሻ (shithole) ያልሆነች አገርና መሪ ጥራልኝ፡፡ በሙሉ 'ሺትሆል' ናቸው፡፡ በሙሉ ሽንት ቤት ናቸው፡፡ ማንዴላንስ ብትል፣ አሁን እሱ መሪ ነው ብለህ ታስባለህ?አይደለም፡፡›› ብለውኛል ትራምፕ ይላል፡፡

2.ኦባማን በተመለከተ

ጠበቃ ማይክል ኮሐን እንደሚለው ትራምፕ እንደ ኦባማ የሚቀኑበትም፣ የሚጠሉትም ፖለቲከኛ የለም፡፡ ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ንቀትም አለበት፡፡

የጥላቻውን ደረጃ ጠበቃው ሲገልጽ ይህንን ብሏል፡፡

‹‹ትራምፕ በፊት የሪፐብሊካን እጩ ከመሆናቸውም ቀደም ብሎ አንድ ቪዲዮ በትእዛዝ አሰርተው ነበር፡፡ ቪዲዮው ትራምፕ አፓረንቲስ (Apprentice television) በተሰኘውና ያልጣሟቸውን ሰዎች ከሥራ በሚያባርሩበት የገሀዳዊ ቲቪ ትእይንት (Reality show) ኦባማን የሚመስል ሰው እንዲዘጋጅና ያን ሰው መጀመርያ ክበው፣ ክበው ከዚያም እያዋረዱ ሲያባርሩት የሚያሳይ ቪዲዮ ነበር፡፡

ይህ ቪዲዮ ግን ሳይሰራጭ ቀርቷል፡፡ የዚህ ቪዲዮ ዓላማ የነበረውም ትራምፕ ኦባማን በእውን ባይሆንም በምናባዊ ቪዲዮ መበቀል ስለፈለጉ ነበር፡፡

3.ሂስፓኒክ ዘሮችን በተመለከተ

ጠበቃ ማይክል ኮሐን እንደሚለው ትራምፕ በአንድ ወቅት ‹‹መቼም ቢሆን የነዚህ የሂስፓኒኮችን ድምጽ የማገኝ አይመስለኝም፤ ልክ እንደ ጥቁሮች ሁሉ እነሱም ስድ አደጎች ናቸው፡፡ እኔን አይመርጡኝም፡ እመነኝ፡፡ እነዚህ ሂስፓኒኮች የኔ ሰዎች አይደሉም›› ብለዋል፡፡

ትራምፕ በ2019 የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደኔ ሂስፓኒኮችን የሚወድ ማንም አልተፈጠረም ብለው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

4.ኢቫንጀሊካን ክርስትናን በተመለከተ

ጠበቃ ማይክል ኮሐን እንደሚለው በአንድ ወቅት ዶናልድ ፕሬዝዳንት በሆኑ ማግስት የኢቫንጀሊካን ክርስቲያን መሪን በቢሯቸው ‹ትራምፕ ታወር› አግኝተውት ነበር፡፡ ሰውየው ልክ ከቢሮ እንዳሰናበቱት ወደኛ ዞረው፣ ‹አሁን ይሄ ቄስ የሚቀባጥረውን ነገር የሚያምን ሰው አለ?› ብለዋል፡፡

ትራምፕ ጥብቅ የኢቫንጀሊካን አማኝ እንደሆኑ ነው የሚናገሩት፡፡ የኢቫንጀሊካን አማኞችን ድምጽም በከፍተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ ምክትላቸው ማይክ ፔንስም የዚሁ ክርስትና ቅርንጫፍ ጥብቅ አማኝ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

5.ፑቲንን በተመለከተ

ትራምፐ በዓለም ላይ የሚያደንቁት መሪ ቢኖር ፑቲንን ነው ይላል ጠበቃ ማይክል ኮሐን፡፡

ምክንያቱን ሲገልጽም፡ ትራምፕ በአንድ ወቅት የነገሩትን ያስቀምጣል፡፡

‹‹ፑቲን አንድን ትልቅ አገር ልክ እንደራሱ ንብረት፣ እንደግል ኩባንያው ሲመራ አይገርምም? ታድሎ! ልክ እንደኔ ትራምፕ ኩባንያ እኮ ነው ራሺያን የሚገዛት…››

ኮሐን እንደሚለው ትራምፕ ፑቲንን ማድነቃቸው እንዳለ ሆኖ ግን ሆን ብለው ፑቲንን ይኮፍሱት ነበር፡፡ ይህም ከሱ ጥቅም ለማግኘት፡፡

በ2016 ምርጫ ድምጽ ካጣሁ ከሱ ብዙ ገንዘብ አገኛለሁ በሚል ደጋግመው ፑቲንን ይኮፍሱት ነበር ብሏል ጠበቃ ኮሐን።

6.ቅምጣቸውን በተመለከተ

የወሲብ ፊልም ኮከቧ ስቶርሚ ዳንኤልስን በተመለከተም ጠበቃው ይህንን ጽፏል፡፡

በ2016 የትራምፕ ቅምጥ ነበረች የምትባለውን ስቶርሚ ዳንኤልስን አግኝቻት ነበር፡፡ ይህን ገንዘብ ስጣትና እከፍልሀለው ያለኝ ትራምፕ ነው፡፡

ገንዘቡ የሚሰጣት ከትራምፕ ጋር ስለነበራት ግንኙነት ትንፍሽ እንዳትል ነው፡፡ (ሀሽ መኒ ይሉታል እነሱ፡፡)

ትራምፕ እንዲህ ብለውኝ ነበር፤- ‹‹እኔ ይህን ገንዘብ ልሰጣት አልፈለኩም ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ በጣም ብዙ ጓደኞቼ ስጣትና ተገላገል ብለውኝ ነው፡፡

ከሷ ጋር አንሶላ የመጋፈፍ ቅሌቴ ቢወጣብኝ ደጋፊዎቼ ምን እንደሚሰማቸው አላውቅም፡፡ ነገር ግን ከእውቅ የወሲብ ፊልም ተዋናይት ጋር መተኛቴ የሚያዝናናቸው ይመስለኛል‹‹ ብለውኛል ብሏል ጠበቃ ኮሐን፡፡"

ጠበቃ ኮሐን ማን ነበር?

ማይክል ኮውን ዶናልድ ትራምፕ ከነበሯቸው የግል ጠበቆች ዋንኛው ነው፡፡ የትራምፕ የሁሉ ጉዳዮች አሰናጅ ተብሎም ይታወቃል፡፡

ነገር ግን ኋላ ላይ ተቀያይመዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ለኮንግረስ ብዙ ምስጢር በመዘርገፉ ትራምፕ ጠልተውታል፡፡

በ2018 ግብር አጭበርብረሃል፣ ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተሀል፣ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ገንዘብ መዝብረሀል በሚል ነው የታሰረው፡፡

ጠበቃ ማይክል ኮሐን አሁንም እስሩን አልጨረሰም፡፡ 3 ዓመት ነው የተፈረደበት፡፡ ሆኖም በኒውዮርክ በሚገኘው ቤቱ ውስጥ ሆኖ ቀሪውን የእስር ጊዜ እያሳለፈ ነው፡፡ ይህም የሆነው ኮሮና በእስር ቤት ሊዛመት ይችላል በሚል ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ ጠበቃቸውን ማይክል ኮሐንን ‹‹አይጥ›› እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡