የሮበርት ኬኔዲ ገዳይ በምህረት ሊፈታ ይችላል ተባለ

ሲርሃን ሲርሃን
ታትሟል

የካሊፎርኒያ የምህረት ቦርድ በአውሮፓውያኑ 1968 የፕሬዚዳንት እጩ የነበሩትን ሮበርት ኬኔዲን ገዳይ በምህረት እንዲፈታ ወስኗል።

ሲርሃን ሲርሃን፣ ሮበርት ኬኔዲ በሎስ አንጀለስ በሚገኝ አንድ ሆቴል ንግግር ካደረጉ በኋላ ተኩሶ በመግደል የታሪክን አካሄድ ለውጧል የተባለ ግለሰብ ነው። ለዚህም 53 አመታትን በእስር ኣሳልፏል።

ነገር ቦርዱ ግለሰቡ የሕዝብ ስጋት አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ድምፅ ቢሰጥም ግለሰቡ ለመፈታተቱ ዋስትና አይሆንም ተብሏል።

የመጨረሻ ውሳኔውም በካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም እጅ ወድቋል።

ዴሞክራቱ በአሁኑ ጊዜ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ መግባታቸውም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሏል።

ሲርሃን ለምህረት ቦርዱ "ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አልፏል" በማለት ተናግሯል።

"ያ ወጣት፣ ሃሳብ አልባ ልጅ ከእንግዲህ የለም" በማለት አስረድቷል።

የግለሰቡን የምህረት ሂደት እንዲዘግብ በብቸኝነት የተጋበዘው አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው "ሴናተር ኬኔዲ የዓለም ተስፋ ነበር ። እሱን በመጉዳቴ በርካቶችን ጎድቻለሁ ይህንንም አሰቃቂ ሁኔታ መፈፀሜ ያሳምመኛል" በማለት ተናግሯል።

በሎስ አንጀለስ የሚገኘው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ግለሰቡ ከእስር መፈታቱን ለመቃወም እንደማይንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የ77 ዓመት እድሜ ባለጸጋ የሆነው የፍልስጥኤሙ ተወካጅ ሲርሃን ምህረት ሲጠይቅ ለ 16ኛ ጊዜ ነው።

ግለሰቡ ከታሰረ በኋላ እንደተናገረው በወቅቱ ሴናተር የነበሩት ሮበርት ኬኔዲ ላይ ጥቃቱን የፈፀመው አሜሪካ ለእስራኤል በምታደርገው ድጋፍ ጋር ተያይዞ ነው ብሎ ነበር። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለ ጥቃቱ ምንም እንደማያስታውሰ ተናግሯል።

የቦርዱ ውሳኔ የመጣው ሁለት የኬኔዲ ልጆች የአባታቸውን ገዳይ እንዲፈታ ለምህረት ቦርዱ ይግባኝ ከጠየቁ በኋላ ነው።

"ለራሳቸው ወይም ለአለም ስጋት የማይሆን ማንኛውም እስረኛ መፈታት አለበት ብዬ አምናለሁ" በማለት ዳግላስ ኬኔዲ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ መናገሩም ተገልጿል።

ሲርሃን ሲርሃን ማን ነው?

ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት እጩነት ቀርበው የነበረውን ሮበርት ኬኔዲ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው አምባሳደር ሆቴል በነበሩበት ወቅት ሶስት ጊዜ ሲርሃን ሲርሃን ተኩሶባቸዋል።

ወቅቱ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1968 ሲሆን በሆቴሉ ማዕድ ቤት የተተኮሰባቸው የቀድሞው የሴኔት አባል ፎበርት ኬኔዲ በወቅቱ ካሊፎርኒያ ላይ የነበረውን የዲሞክራቲክ ፓርቲን ድልን ለደጋፊዎቻቸው እያበሰሩ ነበር ተብሏል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወንድም ሮበርት ኬኔዲ በተተኮሰባቸው በ24 ሰአታት ውስጥ ህይወታቸው አልፏል።

ቀድሟቸው ከአምስት አመታት በፊት በጎርጎሳውያኑ 1963 ከተገደሉት ወንድማቸው ጆን ኤፍ ኬኔዲም አጠገብ ተቀብረዋል።

ሲርሃን ሲርሃን በመጀመሪያ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን ካሊፎርኒያ የሞት ቅጣትን ስታስቀር ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀየረ።

የዮርዳኖስ ዜግነት ያለው ሲርሃን ትውልዱ ፍልስጥኤማዊ ሲሆን ስለ ተኩሱም ሆነ ስለ ግድያው ምንም ነገር እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር።

በጎርጎሳውያኑ 1967 በነበረው የስድስቱ ቀናት ጦርነት ኬኔዲ ለእስራኤል ባደረጉት ድጋፍ እንደከዳን ይሰማኛል በሚል ለአንድ ሚዲያ ተናግሯል ተብሏል።