በሉትዌንያ ከአንድ ኪሎ በላይ ብረታ ብረቶች ከሆዱ ውስጥ የወጣለት ግለሰብ

ብረታ ብረቶች
ታትሟል

ከአንድ የሉትዌንያ ዜጋ ሆድ ውስጥ ከአንድ ኪሎ በላይ የሚመዝኑ የተለያዩ አይነት ብረታ ብረቶች መውጣታቸውን የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ከግለሰቡ ሆድ ውስጥ በቀዶ ህክምና ብረታ ብረቶቹን ያወጡት ሐኪሞች እንዳሉት ሚስማሮችን፣ ቡሎኖችንና ቢላዎችን ማውጣት ችለዋል።

ዶክተሮች እንዳሉት ግለሰቡ የአልኮል መጠጥ ካቆመ በኋላ ለአንድ ወር ያህል የተለያዩ ብረታ ብረቶችን ሲውጥ ቆይቶ እንደነበር ደርሰውበታል።

ክላይፔዳ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚገኘው ሆስፒታል ውስጥ በተደረገው ቀዶ ህክምና ወቅት ከግለሰቡ ሆድ ውስጥ ከተገኙት ብረቶች መካከል 10 ሴንቲ ሜትር ድረስ የሚረዝሙ እንዳሉበት ተዘግቧል።

ቀዶ ህክምናውን ያደረጉት ዶክተር ሳሩናስ ዳይሊዴናስ ከአንድ ኪሎ በላይ የሚመዝኑትን ብረታ ብረቶች ከግለሰቡ ሆድ ውስጥ ካወጡ በኋላ እንደተናገሩት ያጋጠማቸውን "የተለየ ጉዳይ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

ከግለሰቡ ሆድ ውስጥ ብረታ ብረቶቹን ለማውጣት ሦስት ሰዓታትን የፈጀ ቀዶ ህክምና የተደረገ ሲሆን አንድ የቀዶ ህክምና ትሪ ሙሉ ብረት መወገዱን የዩንቨርስቲው ሆስፒታል ይፋ ባደረገው ፎቶ ላይ ታይቷል።

ግለሰቡ ወደ ሆስፒታል በአምቡላንስ የመጣው እጅግ ከባድ የሆድ ህመም ካጋጠመው በኋላ ሲሆን፤ ከቀዶ ህክምናው በኋላም ጤንነቱ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ነገር ግን አሁንም በሆስፒታል ውስጥ ሆኖ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።