የቀድሞው ከፍተኛ ባለሥልጣንና ጄነራል ኮሊን ፓውል በኮሮናቫይረስ ምክንያት አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ኮሊን ፓውል በኮሮናቫይረስ ምክንያት ባጋጠማቸው የጤና ዕክል ምክንያት በ84 ዓመታቸው ማረፋቸውን ቤተሰቦቻቸው ገለጹ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የበላይ በመሆን ከ20 ዓመት በፊት በጆርጅ ደብሊው ቡሽ የተሾሙት ኮሊን ፓውል ለኃላፊነቱ የመጀመሪያው አፍሪካ አሜሪካዊ ናቸው።
ፓውል የውጭ ጉዳይ ኃላፊነትን ከመያዛቸው በፊት የአሜሪካ ከፍተኛው ወታደራዊ መኮንን በመሆን የተለያዩ ዘመቻዎችን መርተዋል።
ከቤተሰባቸው የወጣው መግለጫ "ድንቅ እና አፍቃሪ ባል፣ አባት፣ አያት እና ታላቅ አሜሪካዊውን አጥተናል" ብሏል።
ጨምሮም ኮኒን ፓውል ሆስፒታል ውስጥ ሳሉ ለተደረገላቸው እንክብካቤ ቤተሰቦቻቸው የህክምና ባለሙያዎቹን አመስግነዋል።
ኮሊን ፓውል ለዘብተኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የነበሩ ሲሆኑ በአውሮፓውያኑ 2008 ባራክ ኦባማ ለፕሬዝዳንትንት ሲወዳደሩ ከፓርቲያቸው በተቃራኒ ኦባማን በይፋ ደግፈው ነበር።
ፓውል ከጦር መሪነታቸውና ከውጭ ጉዳይ ሥልጣናቸው በተጨማሪ በአሜሪካ ቀዳሚ ለሚባሉ ፖለቲከኞች ወታደራዊ አማካሪ በመሆን ሰርተዋል።
ፓውል ቬትናም ዘምተው አገራቸውን ሲያገለግሉ የቆሰሉ ሲሆን በዚያ ዘመቻ ወቅት ያካበቱት ልምድ በቀጣይ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ህይወታቸው ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ነበረው።
ነገር ግን አሜሪካ ኢራቅን ልትወር ስትነሳ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ቀርበው ያደረጉት ንግግርና በኋላ ላይ ወታደራዊ ዘመቻው በተሳሳተ የደኅንነት መረጃ ላይ የተመሰረተ መሆኑ መገለጹ በታሪካቸው ላይ ጥቁር ነጥብ እንደጣለ ይነገራል።
ይህንንም በተመለከተ በአውሮፓውያኑ 2005 ላይ ለኤቢሲ ኒውስ ቴሌቪዥን "የሚያም ነበር። አሁንም ያማል" በማለት ሁኔታው የፈጠረባቸውን ጸጸት ተናግረው ነበር።
































