የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አነሳ

የፎቶው ባለመብት, House of Peoples Representatives of FDRE
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት በመላው ኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በዛሬው ዕለት የካቲት 08/2014 ዓ.ም በይፋ አነሳ።
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛው ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላለፉት ሦስት ወራት ያህል ተግባራዊ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
በዚህም ስብሰባ ላይ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማንሳት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በ63 ተቃውሞ በ21 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲያጥር ምክንያት የሆነውም ለአገሪቱ ስጋት የነበረው "የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት አደጋ" መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱ መሆኑም ተገልጿል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ህወሓት እና አጋሮቹ የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የደቀኑትን አደጋን ለመከላከል እንዲያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014ን ያወጀ ሲሆን፣ ይህ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 መጽደቁ ተገልጾ ነበር።
አዋጁ በጸደቀበትም ወቅት በአገሪቱ የተደቀነውን የህልውናና እና የሉዓላዊነት አደጋ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መከላከል የማይቻል ሆኖ በመገኘቱም እንደነበር ተጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት ያለውን ስጋት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ተግባር መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱም ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች ከተቀየሩ እና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይቻላል ብሎ ካመነ የስድስት ወር ጊዜው ሳይጠናቀቅ ጊዜውን የማሳጠር ሥልጣን እንደተሰጠውም ተጠቅሷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸው ጅምር ሥራዎች ካሉ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርግ ተወስኗል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረው ጦርነት ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በመንግሥት በአሸባሪነት ከተፈረጁት አማጺያን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች መታሰራቸው ይታወሳል።
































