የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ካለ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ኮሚሽነሩ አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Ebs
መንግሥት በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው እንደሚለቁ ከቀናት በፊት የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናገሩ።
የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ ይህንን ያሉት የካቲት 16/2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሥራ መጀመሪያ ትውውቅ ፕሮግራም በተካሄደበት ወቅት መሆኑን ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
በዚህ ኮሚሽን አባል ሆነው እንዲሰሩ ኃላፊነት የሰጣቸው ሕዝቡ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሰብሳቢው ኃላፊነት በተሞላው መንፈስ ለመስራትና ከሚዲያውና ከሌሎች አጋላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም መናገራቸው ተገልጿል።
አክለውም ባደረጉት ንግግር የአስፈፃሚው አካል ወይም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም በኮሚሽኑ አሰራር ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚኖር ከሆነ ግን ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው እንደሚለቁ ማሳሰባቸውን ከምክር ቤቱ ካገኘነው መግለጫ መረዳት ተችሏል።
በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የትውውቅ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት በመስራት የተሰጠውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
"ፖለቲካ ከአገር በላይ ስላልሆነ" ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የተሰጠውን ኃላፊነት ገለልተኛ በመሆን ታሪካዊ ሥራ ሰርቶ ማለፍ እንደሚገባው ማስገንዘባቸው ተገልጿል።
በምክክሩ የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንድ አካል ሊታዩ እንደሚገባ ያብራሩት አፈ ጉባኤው የምክክሩ ባለቤት ሕዝቡ በመሆኑም ትክክለኛ ውሳኔ የሚጠበቀውም ከሕዝብ ነው ማለታቸውም ሰፍሯል።
በዚህ ትውውቅ ፕሮግራም ላይ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮዎችን በማካተት እና በሕዝቡ መካከል በርካታ የባህል ትስስሮች ስላሉ እድሉን ለሕዝቡ መስጠት ይገባል ሲሉ የኮሚሽኑ አባላት መናገራቸው ተገልጿል።
በተጨማሪ ሕዝቡን በማወያየት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች በውይይት በሚፈቱበት ሁኔታም ላይ አበክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ሂደትን የሚመራና የሚያስተባብር አካል ለማቋቋም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ጥቆማ መካሄዱ ይታወሳል።
ከጥቂት ወራት በፊት ለሕዝብ በቀረበ ጥሪ መሠረት 632 ዕጩዎች ለኮሚሽኑ አባልነት በተለያዩ ወገኖች ተጠቁመው ከእነዚህ መካከልም ኮሚሽኑን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መስፈርቶች መሠረት 42ቱ ተለይተው ኅብረተሰቡ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ዝርዝራቸው ይፋ ሆኖ ነበር።
ከዚህ ሂደት በኋላም በተጠቋሚ ዕጩዎቹ ላይ በተዘጋጀው መስፈርት መሠረት ከሕዝብ የሚቀርበው አስተያየት ተገምግሞ የመጨረሻዎቹ 11 ዕጩ ኮሚሽነሮች ተለይተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እንዲሾሙ አድርጓል።
ኮሚሽኑ በአገሪቱ ለዘመናት የቆዩ ናቸው በተባሉ የተለያዩ አወዛጋቢና ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው ወገኖችንና ኃይሎችን በማቀራረብ ውይይት ተደርጓ መግባባት ላይ እንዲደረስ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክክሮችን ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከሰሞኑ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የመንግሥታቸው የስድስት ወራት አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ብሔራዊ ውይይቱና ምክክሩ የሚደረገው በቆሰሉ ታሪኮችና ነገ በምንገነባት ኢትዮጵያ ላይ ፟እንደሆነ "የምንገነባው አገር ከሥልጣናችን በላይ ስለሆነ ነው፤ ለወደፊቱ ትውልድ ስለሆነ ነው" ሲሉም አስረድተዋል።
የውይይቱ ሂደት በዋነኝት ሊያካትታቸው የሚገባ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህም ግልፅ፣ የሚገለል ማኅበረሰብ የሌለበትና ሁሉንም ሕዝብ አሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።
እንደ ምሳሌ የጠቀሱት በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን አንቀፅ 39፣ በርካታ ጥያቄ የሚያነሱ ፓርቲዎችን ጉዳይ እንዲሁም የሰንደቅ አላማ ጉዳይን ሲሆን በአሁኑ ወቅት አገሪቱን የሚያከራክሩና የሚያጣሉ ጉዳዮች መቋጫ ሊያገኙ የሚችሉበት ነው ብለዋል።
ውይይት የሚያስፈልገው ሽኩቻ፣ ጦርነትና የፖለቲካ ሽግግር ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው አገሪቷ እያተዘጋጀችበት ያለችውም ምክክር አራት ምዕራፎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።
እስካሁን የተካሄደው ቅድመ ዝግጅት ሲሆን እስካሁን ያለው ብሔርና ፆታን ባሳተፈ መልኩ የተዋቀረ በመሆኑ ጥሩ ጅማሮ ነው ብለዋል።
"በውይይትና በድርድር የሚፈታ ችግር ካለ መንግሥት ለማንም በሩ ክፍት ነው። እኛ የምንጠላው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ሲሆን ነው" ብለዋል።
































