በፈረንሳይዋ ደሴት እስረኛው በጂሃዲስት ከተገደለ በኋላ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

በጥቃቱ የተገደለው እስረኛ
ታትሟል

በፈረንሳይ ሜዲትራኒያን ደሴት በእስር ላይ የነበረው ኮርሲካዊ ብሔርተኛ በአንድ ጀሃዲስት በደረሰበት ጥቃት ህይወቱ ማለፉ ተከትሎ በማረሚያ ቤት ቁጣ ተቀስቀሰ።

ባለስልጣንን በመግደል የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረው የ61 ዓመቱ ኢቫን ኮሎና በስርቤቱ ባለ በካሜሮናዊ ጂሃዲስት እስረኛ ክፉኛ የተደበደበው ከሶስት ሳምንታት በፊት ነበር።

በድብደባው ኮሎናን ራሱን ስቶ በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም ሊተርፍ አልቻለም።

የእረኛው ሞት ከማረሚያ ቤት አልፎ በኮርሲካ ደሴት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሷል።

ኢቫን ኮሎና የሜደትራኒያኗ ደሴት ከፈረንሳይ ነጻ ለመውጣት በምታደርገው ዘመቻ በብዙዎች እንደ ጀግና የሚታይ ነበር።

ኮሎና ወደ እስር ቤት የገባው ከሁለት አስርት አመታት በፊት ሲሆን፤ የኮርሲካ ከፍተኛ ባለስልጣንን እንደ አውሮፓውያኑ በ1998 ተኩሶ በመግደል ነበር ወደ እስር የተላከው።

ኮሎናን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለአምስት ዓመታት ፍለጋ የተደረገ ሲሆን በቁጥጥር ሲውል በተራሮች ላይ እረኛ መስሎ እየኖረ ነበር።

በእስር ቤቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ክፍል ውስጥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት በሽብር ወንጀል ተፈርዶበት በእስር ላይ የነበረው የ35 አመቱ ጂሃዲስት ፍራንክ ኢሎንግ አቤ ጥቃት እንደሰነዘረበት አቃቤ ህግ ገልጿል።

ካሜሮኒያዊው ጂሃዲስት ኮሎና ነብዩ መሀመድን "ሲሳደብ" እና ሲሳለቅባቸው ነበር በማለት በፌስታል ለማፈን እንደሞከረ መርማሪዎች ገልጸዋል።

በኮሎና ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የእስር ቤቱ ባለስልጣናት መከላከል አልቻሉም በሚል በደሴቲቱ ላይ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።

ይህም በደሴቲቱ በአስርት አመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ተቃውሞ ነው ተብሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች 'ነጻነት' የሚል እና የፈረንሳይ መንግሥትን የሚያወግዙ ተቃውሞዎችን ያሰሙ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ ድንጋይ እና ነዳጅ የያዙ ተቀጣጣዮችን ወደ ፖሊሶች ወርውረዋል።

በኮርሲካ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ባስቲያ በተነሳ ሁከት 67 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 44ቱ የፖሊስ አባላት ናቸው።

የናፖሊዮን ቦናፓርት የትውልድ ቦታ በመሆኗ ዝነኛ የሆነች ደሴት፤ ከ18 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የፈረንሳይ ግዛት ነች። ይሁን እንጂ ከፈረንሳይ ነጻነትን ለማግኘት የሚደረግ ትግል እየተጠናከረ መጥቷል።