በጂንካ እና ዙሪያዋ በተፈጠረው ሁከት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

ጂንካ ገበያ
የምስሉ መግለጫ, ጂንካ ገበያ
ታትሟል

ባለፉት ጥቂት ቀናት በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ እና ዙሪያዋ ከዞን አደረጃጀት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ሁከት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አስተዳዳሪው አቶ ንጋቱ ዳንሳ ከሕይወት መጥፋት በተጨማሪ በሌሎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል፤ በንብረት ላይም ውድመት አጋጥሟል ብለዋል።

"በጂንካ እና በዙሪያው ባሉ ከተሞች ቤቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶች አሉ። ቤት የማቃጠል ነገር ነበር። በተሽከርካሪ ላይም ጉዳት ደርሷል። የደረሰውን የጉዳት መጠን አጣርተን ስላልጨረሰን አሁን ላይ መናገር አልችልም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ንጋቱ ከሆነ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት መቆጣጠር ችለዋል።

ደቡብ ምዕራብ ኦሞ ዞን ከ13 በላይ ብሔረሰብ አባላት የሚገኙበት ሲሆን ጂንካ ከተማ የዞኑ ዋና ከተማ ናት።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በከተማዋ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው በንብረታቸው ላይ ውድመት መፈጸሙን የሚዘግቡ ሪፖርቶች በማሕበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ሲሰራጭ ነበር።

የዞኑ አስተዳዳሪ በዞኑ ውስጥ ነዋሪ ከሆኑ ማሕበረሰብ መካከል አንዱ የሆነው የአሪ ብሔረሰብ በዞን የመደራጀት ጥያቄ ከዚህ በፊት አቅርቦ እንደነበረ ያስታውሳሉ።

"ይህ በዞን የመደራጀት ጥያቄ በሂደት ላይ ነው ያለው። ይህ ብቻ ሳይሆን የደቡብ ኦሞ ዞን በራሱ ክልል የመሆን ጥያቄ አቅርቦ ጉዳዩን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አቅርቧል" ይላሉ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔረሰቦችም በወረዳ እና በዞን የመደራጀት ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን ይገልጻሉ።

"በሌሎች ሕዝቦች ውስጥ ያለ ጥያቄ ነው። የአሪ ሕዝብም በዞን እደራጃለሁ፤ መንግሥት ያስቀመጠውን መስፈርት አሟላለሁ በሚል ጥያቄ አቅርቧል። ጥያቄው ችግር ያለው አይደለም፤ ነገር ግን መንግሥት 'የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በመልካም አስተዳደር ሥር እመለከተዋለሁ አሁን አገራዊ ጉዳዮች ስላሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን አቆዩ' ባለበት ሰዓት የአሪ የዞን ጥያቄነት አስፈጻሚ ነን የሚሉ ምሁራን እና ፖለቲከኞች 'ጥያቄው ተከልክሏል' በማለት ወደ አመጽ ለመውሰደ ሞክረው ሁከት ፈጥረዋል።" በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።

አቶ ንጋቱ በአሁኑ ወቅት በጂንካ እና ዙሪያዋ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና ከተማዋን ወደ ቀደመ እንቅስቃሴዋ የመመለስ ሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"የተዘጉ መንገዶች አሉ። መንገዶች እንዲከፈት እየተሰራ ነው። ከተማውን ወደ ቀደመ ሁኔታ ለመመለስ እየጣርን ነው።" ብለዋል።